በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸምን የዲጂታል ጥቃት ለመከላከል…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸምን ማንኛውንም አይነት ጥቃት የማይታገስ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል አሉ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች፡፡
ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን (ኢሊዳ) በሴቶች ጥቃትና መከላከል ሥራ ላይ በትኩረት የሚንቀሳቀስ ሀገር በቀል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶ ነው፡፡
የኢሊዳ ኮፋውንደርና ዋና ዳይሬክተር ዚነት ይመር እንደሚሉት ÷ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት በሴቶች አካላዊ፣ አእምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ጤንነት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳዳራል፡፡
በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት በየጊዜው መልኩን እንደሚቀያየር ጠቁመው አሁን ላይ÷በዲጂታል የሚፈጽም ጾታዊ ጥቃት እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን ለመከላከልን ለመቀነስ ኢሊዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው እህቶች ከችግሩ እንዲወጡና እንዲያገግሙ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢሊዳ በ16 ቀናት የጸረ ጾታ ንቅናቄ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ÷ በዚህም ከት/ቤቶች፣ ከሃይማኖታ ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በትብብር መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ጥቃት ለማስቆም በቅንጅተና በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ከባለድርሻዎች ጋር መግባባት ላይ መደረሱን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በሴቶችና ላይ የሚፈጸም ጥቃት እየተባባሰ በመሆኑ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ያሉት ደግሞ በኢሊዳ የጂቪቪና ሒውማኒታሪያን ዲፓርትመንት አስተባባሪ ሜሪ ካሳዬ ናቸው፡፡
በተለይም በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት የማይታገስ ማሕበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡![]()
በሴቶችና ሕጻናት ላይ ጥቃት በሚያደርሱ አካላት ላይ የሚወሰደውን ሕጋዊ ርምጃ ክፍተት ያለበት በመሆኑ በደንብ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በሴቶችና ሕጻናት ላይ ቴክኖሎጂን በመታገዝ የሚፈጸምን ጥቃት ለመከላከልም ቴክኖሎጂ ላይ መሰረት ያደረግ መፍትሔ መፈለግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለ20ኛ ጊዜ የተከበረውን 16ቱ ቀናት ዓለም አቀፍ የጸረ ጾታዊ ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ አሰራሮችንና የአገልግሎት ሥርዓቶችን በመዘርጋት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በተጎጂዎች ላይ የሚደርሰውን የጤና፣ የማሕበራዊና ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም የሕግ ምላሽ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የዘንድሮው ንቅናቄ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርስን ጥቃት መከላከልና ማስቆም ላይ ትኩረት በማድረግ በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
ንቅናቄው ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ ለተጎጂዎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግና የጾታ ጥቃትን ለማስወገድ ያለመ ነው ብለዋል፡፡