ቤተ ክርስቲያኗ ያከናወነችው የማኅበራዊ ልማት የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ቀይሯል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ልማት የምታደርገው አስተዋጽኦ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀየረ ነው አሉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሸገር ከተማ ለቡ አካባቢ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢኩስታ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጎብኝተዋል።
በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ልማት የምታደርገው አስተዋጽኦ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የቀየረመሆኑን ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያኗ በትምህርት፣ በጤና፣ በመጠጥ ውኃ ልማትና በወጣቶች የቴክኒክ ሥልጠና የምታደርገው የልማት ድጋፍ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የትምህርት ተቋሙ በተለይም የኢትዮጵያን የሕክምና ዘርፍ የመመርመርና የማከም አቅም የሚያሳድግ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በተቋሙ የተመለከቱት ንጽሕና እና ጽዳት የሚደነቅና ለብዙ ተቋማት አርአያ እንደሚሆንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡
ተቋሙ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተሟልተውለት ሁለንተናዊ አገልግሎቱን እንዲጀምር በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ለተቋሙ የሚሆን መሬት በመስጠቱና ተቋሙን በዘመናዊ መሣሪያዎች ለማደራጀት እገዛ ያደረጉ አካላትንም አመስግነዋል።