የኢትዮጵያ ብልፅግና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብልጽግና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እየተሰራ ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
በኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ 2025 ኤግዚቢሽን እና ፎረም ተጀምሯል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት÷ የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (ኮፕ2032) እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ኢትዮጵያ ሰፋፊ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስራዎችን እያከናወነች ነው።
በኢትዮጵያ የተሟላ ለውጥ እና ብልጽግናን ለማምጣት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው÷ ይህ ዘላቂ ልማት እና ለውጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት መለዋወጥ የከተሞች መጨናነቅ እና ዝቅተኛ የኃይል አቅርቦት የልማት ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ ኢትዮጵያ ችግሮቹን በመረዳት መፍትሄ ለመስጠት ከጠረጴዛ ተኮር ወደ ተግባር ተኮር ስራ መሸጋገሯን አብራርተዋል፡፡
በነዳጅ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እንዲሁም የልማት ስራዎችን ከፀሐይ፣ ከሃይድሮ ኤሌክትሪክ እና ከነፋስ ኃይል ልማት ጋር ለማስተሳሰር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ስለአረንጓዴ ልማት የምንጨነቀው ለቀጣይ ትውልድ ስለምናስብ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት የሰጠችው ትኩረት ከራሷ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ውጤቶች የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በሕዝቡ ቆራጥ ስራ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግሥት በዘርፉ የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ በኢትዮጵያ ብክለት ቀናሽ እንቅስቃሴ 2025 ኤግዚቢሽን እና ፎረም የኢትዮጵያን ብክለት ቅነሳ መርሐ ግብር ያግዛል ብለዋል።
በለይኩን ዓለም