Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የተገነቡ 32 የፖሊስና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማት ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባታቸው የተጠናቀቁ 32 አዳዲስ የፖሊስ እና የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ ዛሬ በአዲስ አበባ ፖሊስ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተበሰረበት ዕለት ነው።
በመዲናዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ 32 አዳዲስ የፖሊስ እንዲሁም የእሳትና አደጋ ሥጋት መከላከያ ተቋማት ተመርቀው በይፋ ሥራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በዚህም የፖሊስ መምሪያዎች፣ ጣቢያዎች፣ ካምፖች፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከያ ተቋማት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ነው ያሉት።
ይህ ተግባር በከተማዋ ፖሊሳዊና ድንገተኛ አደጋን የመከላከል አገልግሎቶችን ወደ ሕዝቡ ደጃፍ ይበልጥ ማቅረብ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ነዋሪው በሰላም ግንባታና በአካባቢ ጥበቃ ሒደት ላይ በባለቤትነት ስሜት በንቃት እንዲሳተፍ የሚያስችል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
በተለይም እነዚህ ተቋማት በየአካባቢው መገንባታቸው ወንጀልን ለመከላከልና ድንገተኛ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት የሚሰጠውን የምላሽ ጊዜ በእጅጉ እንደሚያሳጥሩ አመልክተዋል፡፡
ይህም በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመቀነስ ትልቅ አቅም ይፈጥራል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል ከንቲባ አዳነች፡፡
ተቋማቱ መዲናዋ ከደረሰችበት ፈጣን የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲመጣጠኑ ተደርገው ከመገንባታቸው በላይ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ አካታች መሰረተ ልማቶች ናቸው፡፡
እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየባቸው፣ የሕፃናት ማቆያና ክሊኒክን ያካተቱና በዘመናዊ የመረጃ ማሰባሰቢያና የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎች የተደራጁ እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡
ከንቲባ አዳነች መሰል ፋይዳቸው ጉልህ የሆኑ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ እውን እንዲሆኑ ላስቻሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.