በባሕር በር ጉዳይ ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በባሕር በር ጉዳይ ሁሉም በጋራ ሊቆም ይገባል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ክንውኖች በተመላከተ ማብራሪያ የሰጡት ጌዲዮን (ዶ/ር)÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው ከሚገኙ አብዛኛው ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት መልካም የሚባል መሆኑን አንስተዋል።
ቀጣናው ኃያላን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚሻኮቱበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በተጨማሪም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በመሰረተ ልማት ማለትም በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በባቡር እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የማስተሳሰር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የባሕር በር ጥያቄው መልስ እንዲያገኝ የረጅም ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ባገናዘበ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ የኢትዮጵያን አጀንዳ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የማስገንዘብ ስራዎች መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን በማንሳት÷ ጥያቄው ከአንድ መንግሥት ወይም ፓርቲ የሚሻገር እንደሆነም አስረድተዋል።
በመሆኑም ይህንን ሀገራዊ ጉዳይ የጋራ አጀንዳ አድርጎ በማስቀጠል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥያቄውን ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት