አወዛጋቢው ኮከብ ማሪዮ ባላቶሊ…
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በነውጠኛ ባህሪው እና በአወዛጋቢ ድርጊቶቹ የሚታወቅ ተጫዋች ነው ማሪዮ ባላቶሊ፡፡
ማሪዮ ባላቶሊ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሕይወቱን የጀመረው በሀገሩ ክለብ ሉሜዛን ሲሆን÷ ከዚያ በመቀጠል ለኢንተር ሚላን፣ ማንቼስተር ሲቲ፣ ኤሲሚላን እና ሊቨርፑልን ለመሳሳሉ ታላላቅ ክለቦች መጫወቱ ይታወሳል፡፡
ከጣሊያኑ ክለብ ኢንተርሚላን ጋር በፈረንጆቹ 2009/10 የውድድር ዓመት የሶስትዮሽ ዋንጫ አሳክቷል፡፡
በእንግሊዙ ክለብ ማንቼስተር ሲቲ ለሦስት የውድድር ዓመት የቆየው ባላቶሊ ሲቲ በፈረንጆቹ 2011/12 የሊጉን ዋንጫ ሲያሳካ ትልቁን አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይዘነጋም፡፡
በወቅቱ ማንቼስተር ሲቲ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቱን በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ ሲያረጋግጥ በጨዋታው የማሸነፊያዋን ግብ አጉዬሮ ሲያስቆጥር አመቻችቶ ያቀበለው ባላቶሊ ነበር፡፡
ግብ ካስቆጠረ በኋላ እንደሌሎች ተጫዋቾች ሲደሰት የማይታየው ባላቶሊ ደስታውን ለምን እንደማይገልጽ ሲጠየቅ ግብ ማስቆጠር ስራዬ ነው የሚል ምላሽ በአንድ ወቅት መስጠቱ ይታወሳል፡፡
መኪና ማቆም በሚከለከልበት ቦታ መኪና በማቆም የገንዘብ ቅጣት የሚከፍለው ተጫዋቹ የገዛ መኪናውን ከግንብ ጋር አጋጭቶም ያውቃል፡፡
ጣሊያናዊው ተጫዋች ባላቶሊ በቆዳ ቀለሙ የዘረኝነት ጥቃት በተደጋጋሚ ቢደርስበትም ኮከብ ተጫዋች ከመሆን አላስቆመውም፡፡
ባላቶሊ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቆይታው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ አጀንዳ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በፈረንጆቹ 2010 ማሪዮ ባላቶሊ የጎልደን ቦይ ሽልማትን ካሸነፈ በኋላ ሽልማቱ ይገባኛል በማለት የተናገረ ሲሆን÷ ጋዜጠኞች 2ኛ ስለወጣው ጃክ ዊልሸር ሲጠይቁት ጃክ ዊልሸር የሚባል ተጨዋች እንዳለ አላውቅም በማለት ነበር የመለሰው፡፡
ሜሲ 7ኛ የባሎንዶር ሽልማቱን ባሸነፈበት ወቅት ሜሲ በሻምፒየንስ ሊግ ወሳኝ ጨዋታዎች ላይ ሳይሳተፍ 7 የባሎንዶር ሽልማት ከተሰጠው 3 የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን በተከታታይ ላሸነፈው ክርስቲያኖ ሮናልዶ 20 ባሎንዶር ሊሰጠው ይገባል በማለትም አስተያየቱን ሰጥቶ ነበር፡፡
ማንቼስተር ሲቲ ዩናይትድን 6 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ባላቶሊ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን÷ ግብ ካስቆጠረ በኋላ why always me የሚል ጽሑፍ ያሳየው ተጫዋቹ ለምን እኔን ብቻ የሚለውን ጽሑፍ በትሸርቱ እንደፃፈም መናገር አይፈልግም፡፡
ባላቶሊ ከተጫወተባቸው ክለቦች መካከል በሊቨርፑል እና ኤሲሚላን ያልተሳካ ጊዜ አሳልፏል፡፡
የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እና የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨምሮ የተለያዩ ዋንጫዎችን ያሳካው ባላቶሊ ቀይ ካርድ መመልከት፣ አወዛጋቢ ነገሮችን ማድረግ የሁል ጊዜ ተግባሩ ነበር፡፡
ማሪዮ ባላቶሊ በእግር ኳስ ሜዳ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪም በቀላሉ የሚናደድ ሲሆን የገዛ ቤቱንም አቃጥሏል፡፡
ሀገሩ ጣሊያንን ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2018 ያገለገለው ባላቶሊ ለብሔራዊ ቡድኑ 36 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ለእግር ኳስ ቤተሰብ ለዓመታት ነውጠኝነቱን ሲያሳይ የቆየው ባላቶሊ በ2025 ነበር ከእግር ኳስ ዓለም ራሱን ያገለለው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ