ማንቼስተር ሲቲ ከቼልሲ …
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ20ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ይጀምራሉ፡፡
አስቶንቪላ ከኖቲንግሃም ፎረስት በቪላ ፓርክ ቀን 9:30 ላይ የሚያርጉት ጨዋታ ቀዳሚው መርሐ ግብር ነው፡፡
ከ11 ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ በአርሰናል የተሸነፈው አስቶንቪላ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል፡፡
ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሊጉ የተሸነፈው ተጋጣሚው ኖቲንግሃም ፎረስት ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወልቭስ ከዌስትሃም ዩናይትድ እንዲሁም ብራይተን ከበርንሌይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
የሊጉ ጨዋታ ሲቀጥል ምሽት 2:30 ላይ የሊጉ መሪ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ቦርንማውዝን ይገጥማል፡፡
ያለፉትን አራት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ድል ያደረገው አርሰናል አሸናፊነቱን ለማስቀጠል እና ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
አርሰናል ይህንን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከሆነ ማንቼስተር ሲቲ እሁድ ምሽት ጨዋታውን እስኪያደርግ ድረስ ከሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ከፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በሊጉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ ያልቻለው ባለሜዳው ቦርንማውዝ ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
ነገ የሊጉ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ምሽት 2:30 ላይ ቼልሲን ያስተናግዳል፡፡
በሊጉ ከተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ድል በኋላ ከሰንደርላንድ ጋር አቻ የተለያየው ማንቼስተር ሲቲ ከመሪው አርሰናል ላለመራቅ ይፋለማል፡፡
አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካን ያሰናበተው ቼልሲ በሊጉ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ አራቱን በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲሆን በአንዱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 9 ሰዓት 30 ላይ ሊድስ ዩናይትድ ማንቼስተር ዩናትድን ያስተናግዳል፡፡
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በጨዋታው ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቡድኖቹ እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ዩናይትድ በሦስቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሰዓት ምሽት 12 ሰዓት ላይ ኒውካስል ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ፣ ቶተንሃም ሆትስፐር ከሰንደርላንድ፣ ፉልሃም ከሊቨርፑል እንዲሁም ኤቨርተን ከብሬንትፎርድ ይገናኛሉ፡፡
ሊጉን አርሰናል በ45 ነጥብ ሲመራ ማንቼስተር ሲቲ 41፣ አስቶንቪላ 39፣ ሊቨርፑል 33፣ ቼልሲ 30 እንዲሁም ማንቼስተር ዩናይትድ 30 ነጥብ በመያዝ ከ2ኛ እስከ 6ኛ ድረስ ባለው ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
ወራጅ ቀጠና ውስጥ ዌስትሃም ዩናይትድ በ14 ነጥብ፣ በርንሌይ በ12 እንዲሁም ወልቭስ በ3 ነጥብ ከ18ኛ እስከ 20ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የሊጉን ኮከብ ግብ አስቆጣሪነት የማንቼስተር ሲቲው የፊት መስመር ተጫዋች ኤርሊንግ ብራውት ሃላንድ በ19 ግቦች ሲመራው ኢጎር ቲያጎ በ11 እንዲሁም አንቶኒዮ ሴሜኒዮ በ9 ግቦች ይከተላሉ፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ