Fana: At a Speed of Life!

የዲጂታል መታወቂያ አሁን ባለንበት ዓለም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስርን እየቀየረ ያለ የቴክኖሎጂ አብዮት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዲጂታል መታወቂያ አሁን ባለንበት ዓለም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስርን እየቀየረ ያለ የቴክኖሎጂ አብዮት ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ የፋይዳ መታወቂያን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ፋይዳ ምን ይፈይዳል?

የዲጂታል መታወቂያ አሁን ባለንበት ዓለም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስርን እየቀየረ ያለ የቴክኖሎጂ አብዮት ነው፡፡

በኢትዮጵያም “ፋይዳ” መታወቂያ የዚህ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ አንዱ አካል እየሆነ ሲሆን እንደ ስንጋፖር፣ ህንድ እና ኢስቶኒያ ያሉ ሀገራት የዲጂታል መታወቂያን በመጠቀም አብዛኛዎቹን የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል በመቀየር የዜጎቻቸውን ሁለንተናዊ አገልግሎት በማዘመን ተጠቃሽ ሀገራት ናቸው፡፡

የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት፣ የዲጂታል መታወቂያን ስራ ላይ ማዋል ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ፋይዳ ዜጎች ማንነታቸው ታውቆ ሁሉንም ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት እንዲያገኙ ከማድረጉም ባሻገር የባዮሜትሪክ መረጃዎችን በመጠቀም ማንነትን መጭበርበርንና ሀሰተኛ መረጃዎችን ማዘጋጀት የማይቻል በማድረግ የሀገርን ደህንነት በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክራል።

ፋይዳ በመንግስትና በዜጎች መካከል የሚገቡ ደላላዎችን በማስቀረት፣ አገልግሎቶች ለታለመላቸው እውነተኛ ዜጎች ብቻ እንዲደርሱ በማድረግ ሙስናንና የሀብት ብክነትን የመከላከል ትልቅ አቅም ያለው ዲጂታል ሥራ ነው።”

የአገልግሎቶ አሰጣጥን የምያሳልጥ ይህ ስርዓት፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንድትገነባ መሰረት ይጥላል።

የፋይዳ መታወቂያ ወረቀትንና የተንዛዛ ቢሮክራሲን በማስቀረት የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ዘርፎችን በማቀናጀት ኢትዮጵያ በ2030 ካለመችበት እንድትደርስ የሚያስችላት ትልቅ ብልጽግና ግብ ነው፡፡

እያንዳንዱ ዜጋ በዚህ የታሪክ ጉዞ ውስጥ የፋይዳ መታወቂያ በመያዝ፣ ለሀገሪቱ የዲጂታል ሽግግር ስኬትና ለዘመናዊ አሰራር መስፈን መሰረታዊ ሚና መጫወት ይገባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.