ሕብረተሰቡ በዲጂታል አማራጮች በመጠቀም ግብይት ሊፈጽም ይገባል
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕብረተሰቡ በየአቅራቢያው የሚገኙ የገበያ ማዕከላትንና የዲጂታል ግብይት አማራጮችን በመጠቀም ለአላስፈላጊ ወጪ ሳይዳረግ ግብይት ሊፈጽም እንደሚገባ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳስቧል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የቅዳሜና እሁድ ገበያ ማዕከላትን የግብይት ሂደት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ ህብረተሰቡ የበዓል ሰሞንን ትክክለኛ መረጃ ላይ በመመርኮዝ በየአቅራቢያው የሚገኙ የገበያ ማዕከላት አማራጭን በመጠቀም መገበያየት ይችላል።
የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም ግብይት መፈጸም የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ህብረተሰቡ የዲጂታል ግብይት እንዲጠቀም አስገንዝበዋል።
የገበያ ማዕከላቱ መሰረታዊ ሸቀጦችና የቁም እንስሳት ግብይት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው፤ ሕብረተሰቡ ያለሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት የተረጋጋ ግብይት ማከናወኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በሁሉም አካባቢ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ማዕከላትን በማስፋት፣ በማዘመን፣ አቅርቦትና ፍላጎትን በማመጣጠን የህዝቡን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።
በየሻምበል ምህረት