Fana: At a Speed of Life!

የጤና አገልግሎትን ለማዘመን የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር አብሮ ሊሰራ ይገባል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መንግሥት የጤና አገልግሎቱን ለማዘመን በሚሰራው ስራ የግሉ ዘርፍ በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

ከንቲባዋ ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች የታገዝ የላቀና ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የተገነባውን ሀባሪ የጤና ፕላዛን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።

ከንቲባ አዳነች በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሀባሪ የጤና ፕላዛ ዋነኛ ግብ አድርጎ የተነሳው በህክምና ምክንያት ወደ ወጭ ሀገራት የሚደረገውን ጉዞ ማስቀረት ብሎም ከጎረቤት ሀገራት ታካሚዎችን መሳብ ነው።

በዚህም የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ዜጎች የህክምና አገልግሎትን ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገራት ለመሄድ የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሪ መቆጠብ ያስችላል ብለዋል።

መንግሥት ለጤና ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አንስተው÷ ዜጎች በሚፈለገው ልክ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የግሉ ዘርፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ የጤና አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ እና ተደራሽ እንዲሆን ዲጂታል አገልግሎቶችን በመተግበር ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ዕውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

እንደዚህ አይነት ደረጃቸውን የጠበቁ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ኢትዮጵያን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በህክምና ማዕከሉ የተለያዩ ስፔሻሊቲ እና ሰብስፔሻሊቲ ሀኪሞች እንዳሉትና በውጭ ሀገራት ብቻ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ የገለጹት ደግሞ የሀባሪ የጤና ፕላዛ መስራች ዶ/ር አኸዛ ጠዓመ ናቸው።

የጤና ፕላዛው መገንባት መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሰጠው ሰፊ ዕድል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በነፃነት ፀጋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.