Fana: At a Speed of Life!

የትምህርትን ጥራት ማሻሻል የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርትን ጥራት በመሰረታዊነት ማሻሻል የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የለውጥ ጉዞና ፍኖተ ካርታን የሚቃኝ የውይይት መድረክ በባሌ ሮቤ ተካሂዷል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፥ በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሚሰሩ ሥራዎች ውጤት እንዲያመጡ የባለሙያዎች እና የባለድርሻዎች ሚና ከፍተኛ ነው።

ዘርፉን ከወደቀበት ማንሳት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት በመሆኑ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲሰምሩ የባለድርሻዎች ተሳትፎ መጠናከር አለበት ብለዋል።

በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘርፉን በማሸጋገር ለሀገራዊ ለውጥ እገዛ እንዲያደርግ የተለያዩ ሪፎርሞች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

በአጠቃላይ የትምህርትን ጥራት በመሰረታዊነት ለማሻሻል የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የትምህርት ማኅበረሰቡ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ አደራ መወጣት አለበት ብለዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሃብቶችና የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎችን በምርምር በመደገፍ ለማህበረሰቡ ጥቅም እንዲያውል ትኩረት መደረጉን አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታውን በቀጣይ እንዴት መስራት እንዳለበት የውይይት መድረኩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙትን ተግዳሮቶችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታ አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.