Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ እየሰራን እንገኛለን አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ዛሬ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ምክር ቤት የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል ብለዋል።

በውይይቱ በለውጥ አስተሳሰብ የተካተቱ እና የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተቋማት መካተታቸውን ገልጸው፤ በጋራ ከምናከናውናቸው ስራዎች በተጨማሪ በየተቋሞቻቸው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት በምናደርገው ርብርብ የማይተካ ሚና አላቸው ነው ያሉት፡፡

ምክር ቤቱ በአዲሱ ፖሊሲ፣ አዋጅ እና የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ ላይ በመመስረት፤ የሕዝብን አቅም በማስተባበር የማይበገር ማህበረሰብ ለመገንባትና የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ጉዳት በቀነሰ መልኩ ለመከላከል በትጋት ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት ስርዓታዊና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።

ከ2016 ክረምት ጀምሮ በተቀረጹ ፍኖተ-ካርታዎች መሠረት ልመናና ተረጂነትን በምርታማነት ለመተካት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነ አንስተዋል።

በዘላቂነት አስተማማኝ የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ መገንባት፣ የመጠባበቂያ ክምችትን በፌደራልና በክልሎች ማደራጀትና ተፈናቃይ ዜጎቻችን በዘላቂነት ተቋቁመው ወደ አምራችነት እንዲመለሱ ማድረግ የመንግሥታችን ዋነኛ ግብ ነው ብለዋል።

በተለይም የማኀበረሰባችንን የመደጋገፍ መልካም ልምምድ እና የአጋርነት እሴት በማጎልበት በየአካባቢያችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የምናደርገው ርብርብ ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል በማለት አስገንዝበዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ጉዟችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በዕውቀትና በጥበብ መሻገርን ይጠይቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም በመደመር ዕይታና በጠንካራ አመራር ለማሳካት ከስምምነት ላይ ደርሰናል ብለዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንደ ሀገር መላውን ማህበረሰብ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ማስቀመጡንም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.