Fana: At a Speed of Life!

የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር አቅማችንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር የህልውና ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ በዘርፉ አቅማችንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

‘የኤሌክትሮማግኔቲክ ስፔክትረም ልዕልና ለሀገር ሉዓላዊነት’ በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያው ሀገራዊ የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር ወርክሾፕ ተካሂዷል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዝግጅቱ ላይ እንዳሉት፤ በዘመናዊ ውጊያ የህልውና ጉዳይ በሆነው የኤሌክትሮኒክስ ዋርፌር መስክን ለማላቅና ሀገራዊ አቅምን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ከምድር፣ ከባህር፣ ከአየር ሀይልና ከሳይበር በተጨማሪ የኤሌክትሮኒክስ ስፔክትረም ልዕልናን በማረጋገጥ ለሀገራዊ ሉዓላዊነት ማዋል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ብቃት ያለው የሰው ሀይል ለማደራጀት እና ዘመኑን የዋጁ ትጥቆችን ለመታጠቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ሀገራችን እየተገበረችው ያለው የዲጅታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ተበታትነው ያሉ ሀገራዊ አቅሞችን በማሰባሰብ መስራትና በራስ አቅም ማምረት እንደሚገባ አመልክተው፤ ወርክሾፑ በዘርፉ ያለንን ልምድ በመቀመርና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለመራመድ ፅኑ መሰረትን የጣለና ታሪካዊ ነው ብለዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው፤ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ሁኔታ የቴክኖሎጂ የበላይነት ያለውና ስፔክትረሙን የሚቆጣጠር ሀይል ነገሮችን እንደሚቆጣጠር አስገንዝበዋል።

የሀገራችንን እውነተኛ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ ተወዳዳሪ መሆን ሲቻል ብቻ ነው በማለት ገልጸው፤ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስገንዘባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.