ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት የወጣቶች እና የሲቪክ ማህበራት ሚና …
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ እንዲካሄድ የወጣቶች እና የሲቪክ ማህበራት ሚና ከፍተኛ ነው አለ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶት አደረጃጀት፡፡
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በመተባበር በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወጣቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ላለፉት ሶስት ቀናት በባቱ ከተማ የተሰጠው ስልጠና ተጠናቅቋል፡፡
በስልጠና መድረኩ ከክልሉ ሁሉም ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ሊግ ኃላፊ ወጣት ደረጄ አበራ እንዳለው÷ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በህብረተሰቡ በተለይም በወጣቶች እና በሲቪል ማህበራት የነቃ ተሳትፎ ነው፡፡
በምርጫ ሂደቱ የሲቪክ ማህበራት በህግ፣ በፍትሕ እና በታማኝነት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አንስቷል።
የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ከሊፋ ሀሰን በበኩሉ÷ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መሰረት እንዲጥል ወጣቶች በቂ ግንዘቤ ይዘው በንቃት መሳተፍ አለባቸው ብሏል።
ለዚህ ደግሞ የሲቪክ ማህበራትን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክቷል።
ወጣቶች በክልሉ ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የድርሻቸውን በማበርከት ላይ እንደሆኑ ለፋና ዲጂታል የገለጹት ደግሞ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ከድር እንዳልካቸው ናቸው።
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለብሔራዊ ጥቅም መረጋገጥ የወጣቶች አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወጣቱን በስፋት ለማሳተፍ የሚያስችል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ገለልተኛ እንዲሆን የወጣቶች ድርሻ የጎላ እንደሆነና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።