የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት በእቅዱ መሠረት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ለኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ጉልህ አበርክቶ ስለሚኖረው በእቅዱ መሠረት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመንገድ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዟችን ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ዛሬ የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት የሚገኝበትን የስራ ሂደት በተመለከተ ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ የስራ ሂደት እየተከናወኑ የሚገኙ የሰው ኃይል ዝግጅት እና የማሽነሪና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት ምን እንደሚመስል መታየቱን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የመስክ ዝግጅት እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ምን ይመስላሉ የሚሉትን አይተናል ብለዋል።
የሚኤሶ – ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ለከባድ የጭነት መኪኖች አዳጋች የነበረውን መንገድ ምቹ በማድረግ፣ የወጪና ገቢ ንግዳችንን ያቀላጥፋል፤ በቀጠናዊ ትስስር ረገድ ያለንን ሚናም ያጎለብታል ሲሉ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የኢኮኖሚያችንን ተወዳዳሪነትና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ጉልህ አበርክቶ የሚኖረው በመሆኑ በተያዘለት እቅድ መሠረት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይገባል በማለት አሳስበዋል።