Fana: At a Speed of Life!

ውትድርና ጀግንነትንና ስብዕናን ተላብሶ መሠናክሎች ሳይበግሩት በጽናት መቆምን ይጠይቃል – ሌ/ጄ ሹማ አብደታ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ውትድርና ጀግንነትንና ስብዕናን ተላብሶ ሠው ሰራሽና የተፈጥሮ መሠናክሎች ሳይበግሩት በጽናት መቆምን ይጠይቃል አሉ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌ/ጄ ሹማ አብደታ፡፡

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል ለወራት ያሰለጠናቸውን መሠረታዊ ወታደሮች በዛሬው ዕለት በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።

ሌ/ጄ ሹማ አብደታ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ተመራቂዎቹ የመሠረታዊ ውትድርናን እና የመሠረታዊ ኮማንዶ ምልመላ መስፈርቶችን ያሟሉ ናቸው፡፡

የውትድርና ሙያ የጀግንነት ስብዕና የተላበሰ ማንነትን የሚፈልግ ከመሆኑም በላይ ፈታኝ ለሆኑ ሠው ሰራሽና የተፈጥሮ መሠናክሎች ሳይበገሩ በፅናት መቆምን ይጠይቃል ብለዋል።

ይህ ሲሆን በሚያልፍ ሕይወት የማያልፍ ታሪክን በመጻፍ በዜጎች ልብ ውስጥ በትውልድ ቅብብሎሽ ለዘለዓለም መኖር እንደሚቻል አውስተዋል፡፡

ተመራቂ ወታደሮች በቀጣይ ከኮማንዶ፣ ከአየር ወለድ፣ ከልዩ ኃይልና ፀረ ሽብር እንዲሁም ከሪፐብሊኩ የጥበቃ ኃይል ጋር ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን ስልጠና በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝና የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል አመራርና አባላት ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በገጠሟት ጊዜ ሁሉ አለኝታነታቸውን በተግባር ያረጋገጡ የቁርጥ ቀን ልጆች እንደሆኑ መጥቀሳቸውንም የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል አዛዥ ብ/ጄ ቦጃ አጋ በበኩላቸው ÷ ተመራቂዎቹ በቆይታቸው ጠንካራ የአካል ብቃት፣ የተኩስና የተለያዩ የውጊያ ስልቶችን በቀንና በሌሊት የተማሩና በልምምድ ያዳበሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተመራቂዎቹ የሥነ ልቦና እና የጤና ትምህርትንየቀሰሙ መሆናቸውን ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.