የቄራዎች ድርጅት ለገና በዓል ከ5 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት ተዘጋጅተዋል አለ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመጪው የገና በዓል ከ5 ሺህ በላይ የእርድ እንስሳት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፡፡
የድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙልነህ ደሳለኝ እንዳሉት ÷ ለገና በዓል በዋናው ቄራና አቃቂ ቅርንጫፍ ከ5 ሺህ በላይ ጤንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት እርድ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ለእርድ ከሚጠበቁት እንስሳት መካከል 3 ሺህ በሬዎች ሲሆኑ÷ 2 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ በጎችና እና ፍየሎች ናቸው፡፡
ለሕብረተሰቡ የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የእርድ ክፍል፣ የእንስሳት ማቆያ እና የሥርጭት ተሽከርካሪዎች ጥገና እና ዕድሳት መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
ከ40 በላይ ስጋ ጫኝ መኪናዎች ዝግጁ ናቸው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ÷ ሌሎች በርካታ ድጋፍ ሰጪ ተሽከርካሪዎች ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዜጎች ስጋ ለመግዛት ወደ ልኳንዳ ቤቶች ሲያመሩ በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የታረደ መሆኑንና ስጋው ላይ የማረጋገጫ ማሕተም መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የሚሰጠው የእንስሳት እርድ አገልግሎት ኃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ የሚከናወን መሆኑንም አመልክተዋል፡፡