በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ የተደመረ ትውልድ ለመፍጠር ይሰራል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ የተደመረ ትውልድ ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ “የምሁራን ሚና ለሀገራዊ ብልጽግና” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ከምሁራን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ÷ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል መብት እና ዕድል አለው፤ ተደምረን ሀገራችንን ማበልጸግ አለብን ብለዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከግቢያቸው ባሻገር ሄደው በመስራት ተፅዕኖ መፍጠር እንዳለባቸው ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡
ምሁራን ከመንግሥት ብዙ መጠበቅ እንደሌላባቸው ገልጸው ÷መንግሥት የራሱ ሚና ቢኖረውም ምሁራን መትጋት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
ምሁር ችግር ፈቺ ስራ ከሰራ መንግሥት ራሱ ፈልጎ እንደሚያገኘውና እዚህ ያለው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውጪም ተፈላጊነቱ እንደሚጨምር አስገንዝበዋል፡፡
ሀሳብ ካለ መንግሥት በየትኛውም ሁኔታ ለምሁራን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷የሚመጣው ሀሳብ ግን የሚጨበጥ፣ የሚታይ የሚተገበር እና መሬት የሚወርድ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የምሁራን ሚና ለሀገር ብልፅግና ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ ምሁራን በሀገር ብልጽግና ያላቸውን ሚና ለማስፋት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ለመወያየት እና የምሁራንን ሚና ለማጉላት ምሁራን ዕውቀት ያሉትን ነገር መጠየቅ ሊጀምሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በውይይት የሚገኙ ሀሳቦች ተደራጅተው ወደ ፖሊሲ ያድጋሉ ያሉ ሲሆን ÷ካልተወያየን እና የሚጻፍ ነገር ከሌለን የዕውቀት ግብዓት ስለማይኖር እንቸገራለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ውይይት የፖሊሲ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል ገልጸው÷ ለመወያየት ግን ፍላጎት ሊኖረን ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጋራ የተሰጠችን ሀገር ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በቀጣይ 10 ዓመት ውስጥ የተደመረ ትውልድ ይፈጠራል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሁሉም እኩል የሆነባትን ኢትዮጵያ ለመፍጠር መፍቀድ ይጠበቅብናል ያሉ ሲሆን ፤ ይህንን ካላደረግን ግን የምናስበውን ነገር ለማሳካት እንቸገራለን ነው ያሉት፡፡
የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው፤ ምሁራን ታች ወርደው መስራት እና ቀረብ ብለው ማየት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ