Fana: At a Speed of Life!

ልጆች ከቴክኖሎጂ እቃዎች ጋር ያላቸው ያልተገደበ ትስስር የውይይት ባህላቸውን እየጎዳ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ልጆች ከወላጆቻው ጋር ከመወያየት ይልቅ ከቴክኖሎጂ እቃዎች ጋር ያላቸው ያልተገደበ ትስስር የውይይት ባህላቸውን እየጎዳ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ከምሁራን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ÷ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የምሁራን ዋና ሚና ከራስ መታረቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብርና መር ወይም ኢንዱስትሪ መር ከመሆን ይልቅ ብዝሃ ዘርፍ እና ብዝሃ ተዋናይ ያለው መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ለአብነትም ማዕድን ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ይፈጥራል ተብሎ ይታሰብ እንደነበር አስታውሰው÷ ይሁን እንጂ ባለፉት 6 ወራት ወደ ውጪ የተላከው ወርቅ ኢትዮጵያ (ከአምናው ውጪ) እስካሁን በዓመት ኤክስፖርት አድርጋው አታውቅም ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ተደምሮ የዚህኛውን ስድስት ወር የወርቅ ወጪ ንግድ ገቢ እንደማያክል አስረድተዋል፡፡

ኢኮኖሚው ብዝሃ ዘርፍ መሆኑ አዳዲስ ሃብቶች፣ እድሎችና እውቀቶች እንዲመነጩ አስችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ እሳቤውን የትኛውም ምሁር መሞገት፣ መተቸት፣ ማረቅና ማሻሻል እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

ምሁራን አዳዲስ እውቀት እንዳለ አምነው ለመማር የተዘጋጁ መሆን እና ማሕበረሰብን እንዲሁም ሀገርን የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ማመንጨት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የትምህርት ተቋማት በምርምርና ፈጠራ መፍትሄ አመላክች ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቅሰው÷ አዳዲስ እውቀቶችን መፈለግና መቀመር እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግሥት ጥገኝነት ተላቅቀው በራሳቸው የሚተዳደሩ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

መካነ ትምህርት ከጎደለ የምናስበውን ብልጽግና ማሳካት አንችልም፤ ስለሆነም መንግሥት ምሁራን እና መካነ ትምህርት ለሀገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ጠቅሰዋል፡፡

በሚነሱ ሃሳቦች ላይ መከራከርና ለሃሳብ ሉዓላዊነት መገዛት ተገቢና ወቅቱ የሚጠይቀው መሆኑን ጠቅሰው÷ ÷የክርክር ባህል ከፖለቲካ አውድ ባለፈ ማሕበረሰቡ ውስጥ መለመድ እንዳለበትም አብራርተዋል፡፡

የውይይት ባህሉ በምሁራን ዳተኝነትና በዘመኑ ቴክኖሎጂ ምክንያት እየተጎዳ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አሁን ላይ ልጆችና ወላጆች የሚወያዩበት ጊዜ አነስተኛ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

አብዛኞዎቹ ልጆች ክፍላቸውን ቆልፈው ብዙ ጊዜያቸውን ከቴክኖሎጂ እቃዎች ጋር እንደሚያሳልፉ ጠቁመዋል፡፡

ከቴክኖሎጂ እቃዎች ጋር ማውራት የለመደ ሰው ከሰው ጋር ለማውራት ሌላ ልምምድ ይፈልጋል፤ ይህን ለማስቀረትም መስራት ይገባል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት አረንጓዴ ሥፍራዎችን፣ ፓርኮችን ፣ ላይበራሪዎችንና ሌሎች ውይይትን የሚያበረታቱ ዐውዶችን ለማስፋፋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ እኔ ብቻ ልደመጥ የሚል ሳይሆን በውይይት፣ በስክነት እና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር በጋራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.