Fana: At a Speed of Life!

አሰልጣኝ አልወጣልህ ያለው ማንቼስተር ዩናይትድ…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንቼስተር ዩናይትድ 13 የፕሪሚየር ሊግና ሁለት የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ ኦልድትራፎርድን በዋንጫ ያሽቆጠቆጡለትን ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በክብር ከሸኘ በኋላ አሰልጣኝ አልወጣልህ ብሎታል፡፡

በዩናይትድ ቤት 26 ስኬታማ ዓመታትን ያሳለፉት ስኮትላንዳዊው ቆፍጣና ሰው አሰልጣኝነትን በቃኝ ብለው በክብር ከተሰናበቱ ወዲህ ክለቡ የነገሰበትን የሊጉ ዋንጫ ሳያገኝ እንደ ዋዛ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ፈርጉሰን በ2012/13 የውድድር ዓመት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ራሳቸውን ከአሰልጣኝነት ካገለሉ ወዲህ ስድስት ቋሚ አሰልጣኞች ቢፈራረቁም ክለቡን ለሀያልነት ያበቃውን ውጤት ማስቀጠል አልቻሉም፡፡

የዩናይትድን ታላቅነት እንደሚያስቀጥሉ ታምኖባቸው ካሪንግተን የደረሱት የመጀመሪያው ሰው ሌላኛው ስኮትላንዳዊ ዴቪድ ሞይስ ነበሩ፡፡

ዴቪድ ሞይስ የመርሲሳይዱን ክለብ ኤቨርተን ተሰናብተው የታላቁ አሰልጣኝ ምትክ በመሆን ኦልድትራፎርድን ሲረግጡ የዩናይትድ ደጋፊዎች ‘ተመራጩ ሰው’ በማለት ነበር የተቀበሏቸው።

ሆኖም ስኬትን የለመደው ማንቼስተር ዩናይትድ ከኃላፊነታቸው ሲያሰናብታቸው ሙሉ የውድድር ዓመት እንኳን አልታገሳቸውም ነበር።

የሞይስን ስንብት ተከትሎ ደቹ ሊውስ ቫን ሀል በአሰልጣኝነት እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ የክለቡ አንጋፋ ተጫዋች ሪያን ጊግስ በውድድር ዓመቱ የመጨረሻ አራት ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት ክለቡን መምራት ችሎ ነበር።

ከባርሴሎና፣ ባየርን ሙኒክ እና አያክስ አምስተርዳምን ከመሳሰሉ ቡድኖች ጋር ዋንጫዎችን ማሳካት የቻሉት ቫን ሀል ዩናይትድን ወደ ውጤማነት እንደሚመልሱት ብዙ ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።

ነገር ግን እንደተጠበቁት ሳይሆን በመጀመሪያ ዓመት የኦልድትራፎርድ ቆይታቸው ከትችት ማምለጥ አልቻሉም ነበር።

በተለይም በቡድናቸው ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴና የተለየ የአጨዋወት መንገድ የላቸውም በሚል ሲብጠለጠሉ ቆይተው በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የኤፍ ኤ ዋንጫን ማሸነፋቸው ከመሰናበት አልታደጋቸውም ።

ማንቼስተር ዩናይትድ በዴቪድ ሞይስ እና ሊውስ ቫን ሀል እየተመራ ሁለት ደካማ የውድድር ዓመታት ካሳለፈ በኋላ፥ ወደ ውጤታማነት ይመልሱታል በሚል በብዙ የታመነባቸው ጆዜ ሞሪኒሆን ሾመ።

ራሳቸውን “ልዩ ሰው” በማለት የሚታወቁት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ከቼልሲ ጋር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆናቸውን በማስታወስ ሊጉን ጠንቅቀው ያውቃሉ በሚል ከበርካቶች ድጋፍ አግኝተው ነበር።

በስፔኑ ሀያል ክለብ ሪያል ማድሪድና በኢንተር ሚላን ስኬታማ የአሰልጣኝነት ጊዜያትን ማሳለፋቸው ደግሞ እውነትም ልዩ ሰው አስብሏቸው ነበር።

ሆኖም በኦልድትራፎርድ ነገሮች እንዳሰቡት ያልሆነላቸው ሞሪኒሆ ከዴቪድ ሞይስና ቫን ሀል የተሻለ ጊዜ ማግኘት ቢችሉም ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ ቆይታ በኋላ የቀደሙት አሰልጣኞች እጣ ደርሷቸው ተሰናበቱ።

በተለይም ፖል ፖግባን ከመሳሰሉ ተጫዋቾች ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን፥ የተጠበቀውን ውጤት ማምጣት አለመቻላቸው ከክለቡ ጋር እህል ውሃቸው እንዲቋረጥ ሰበብ መሆኑ ይነገራል።

ጆዜ ሞሪኒሆ ዩናይትድን የዩሮፓ ሊግ፣ የካራባኦ እና የኮሙኒቲ ሺልድ ሻምፒዮን ማድረጋቸውና በፕሪሚየር ሊጉ 2ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ማስቻላቸው በኦልድትራፎርድ ለመሰንበት መተማመኛ አልሆናቸውም።

ከሞሪንሆ መባረር በኋላ በጊዜያዊነት የተመደቡትና በኋላም በቋሚነት የተሾሙት የክለቡ የቀድሞ ተጫዋች ኦሌጉናር ሶልሻየር ሦስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ክለቡን መምራት ችለው ነበር።

በእነዚያ ጊዜያት በ2020/21 ዩናይትድ በሊጉ 2ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ያስቻሉ ሰሆን፥ ለዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ ማብቃት ችለው ነበር።

ነገር ግን ሶልሻየርን ካሰናበቱ በኋላ ለማይክል ካሪክ ጊዜያዊ ኃላፊነት ሰጥተው የሰር አሌክስ ፈርጉሰንን ሁነኛ ምትክ ማፈላለጋቸውን የቀጠሉት የክለቡ ኃላፊዎች ራልፍ ራኚክን በጊዜያዊነት መሾማቸው አይዘነጋም።

በመቀጠል ኦልድትራፎርድ የደረሱት ሌላኛው ኔዘርላንዳዊ ኤሪክ ቴን ሀግ ‘የሊቨርፑል እና የማንቼስተር ሲቲ ዘመን በቅርቡ ያከትማል’ በሚለው ንግግራቸው ነበር ራሳቸውን ያስተዋወቁት።

ነገር ግን በአሰልጣኝነት ቆይታቸው እንዳሉትም የማንቼስተር ሲቲና ሊቨርፑልን የበላይነት ከመግታት ይልቅ በክለቡ ታሪክ መጥፎ የሚባሉ ክብረወሰኖችን በመጻፍ ደካማ ጊዜ አሰልፈዋል።

ኤሪክ ቴን ሀግ በቆይታቸው አንድ የኤፍ ኤ እና አንድ የካራባኦ ዋንጫን ማሳካት ቢችሉም በተለይም ቡድናቸው በሊጉ የሚያሳየው የሚዋዥቅ አቋም ለስንብታቸው ሰበብ ሆኗል።

ከዚያም ለምክትላቸው ሩድ ቫኒስትሮይ ጊዜያዊ ኃላፊነት የሰጠው ክለቡ ሩበን አሞሪምን ወደ ኦልድትራፎርድ ማስኮብለሉ ይታወሳል።

በተለይም የጨዋታ ስልታቸውን አልቀይርም በሚለው አቋማቸው ግትር ናቸው በሚል የሚተቹት ሩበን አሞሪም ከ14 ወራት በኋላ ከካሪንግተን ተሰናብተዋል።

ባለፉት ዓመታት ጊዜያዊ አሰልጣኞችን ጨምሮ 10 ያህል አሰልጣኞች የመሩት ማንቼስተር ዩናይትድ በቀጣይስ በየትኛው አሰልጣኝ ወደቀደመ ከፍታው ይመለስ ይሆን የሚለውን ጊዜ ይመልሰዋል።

በኃይለማሪያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.