Fana: At a Speed of Life!

ሁለንተናዊ ትብብር የኢትዮ-ቻይና አጋርነት የጀርባ አጥንት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለንተናዊ ትብብር የኢትዮ-ቻይና አጋርነት የጀርባ አጥንት ነው አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።

አገልግሎቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የኢትዮ-ቻይና የንግድ ልውውጥ ከ13 ቢሊየን ዶላር መብለጡን አመላክቷል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሁለንተናዊ ትብብር የኢትዮ-ቻይና አጋርነት የጀርባ አጥንት ነው። የኢትዮ-ቻይና የንግድ ልውውጡ ከ13 ቢሊየን ዶላር በልጧል።

በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደገ በመምጣቱ በሁሉቱ ሀገራት ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስፋፋ አድርጓል፡፡

በዚህም የሁለትዮሽ የንግድ ለውውጥ ከ13 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የበለጠ ሲሆን ይህም ቻይና ኢትዮጵያን ዋንኛ የንግድ አጋር በማድርግ ግንኙነቷን እያጠናከረች መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከቻይና የምታስገባው ምርት በተጠናቀቀው ዓመት መጀመሪያ ላይ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በመጋቢት ወር ብቻ 1.57 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህም ከባለፈዉ ዓመት ጋር ሲነጻጸር 22% ጭማሪ አሳይቷል።

የውጭ ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰትም ጠንካራ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን፣ ቻይና በማኑፋክቸሪንግ፣ በመንገድና ሕንጻ ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ በመሰማራት ግንባር ቀደም ሀገር ሆና እየሰራች ነዉ፡፡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞን የሚያፋጥኑ የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ተደራሽነት ማስፋፋት በተለይ ከባቡር ሐዲድ ዝርጋታ፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ድረስ የተገኙ ስኬቶች የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ አጋርነትን አጠናክሯል፡፡

የኢኮኖሚ ትብብር የዚህ አጋርነት የጀርባ አጥንት ሲሆን፣ በየካቲት 2017 በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚ እና የንግድ ልዉዉጥ መድረክ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና በአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ኢንዲጠናክር አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ በዚሁ ዓመት ወደ አዲሱ የዓለም የኢኮኖሚ ጥምረት፣ BRICS+ መቀላቀሏ ለዘመናዊነት እና የቻይናን ጨምሮ ለአለም አቀፍ ገበያዎች ተደራሽ የመሆን እድሎችን አስፍቷል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣዉ የሁለትዮሽ ኢኮኖሚ አጋርነት ለሁለቱም ሀገራት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለዉ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ራዕይ ወሳኝ የሆኑ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የገበያዎች መዳረሻ እንዲትሆን እድል የሚያሰፋ ሲሆን፣ ለቻይና ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ እንደ መግቢያ በር ሆና ታገለግላለች፡፡ በተለይ ከቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጋር በማጣጣም የቻይና የረጅም ጊዜ የጋራ ልማት ራዕይን እውን ያደርጋል፡፡

ከዚህ አንጻር የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፣ የፈረንጆቹን የ2026 አዲሱን ዓመት የውጭ አገር ጉብኝታቸውን በአፍሪካ ለመጀመር ታሕሣሥ 30/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ይህ ጉብኝት ቻይና የዓመቱን የመጀመሪያ የዲፕሎማሲ ጉዞ በአፍሪካ አገራት የመጀመር የ36 ዓመታት ረጅም ታሪክ አካል ነዉ፡፡ ጉብኝቱ በተለይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሌሶቶን የሚያካትት ሲሆን ይህም ቻይና ለአፍሪካ ቀንድና ለቀሪው የአፍሪካ አገራት የምትሰጠውን ትኩረት ከማመላከት ባሻገር የኢትዮጵያ-ቻይና ግንኙነት ለአፍሪካ-እስያ ትብብር የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንዲቀጥል የጎላ ድርሻ አለዉ፡፡

ሁለቱ ሀገርት በዛሬው ዕለት በኢኮኖሚ፣ ንግድ፣ መሠረተ ልማት፣ የኃይል አቅርቦት እና ትራንስፖርት ብሎም አዲስ በመፈጠር ላይ ባሉ እንደ ኢ-ኮሜርስ፣ ዲጂታል ኢኮኖሚ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና አረንጓዴ ኃይል ልማት ላይ ትብብራችንን ለማጠናከር ተወያይተዋል።

በአጠቃላይ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጉብኝት በኢትዮጵያና በቻይና መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ስልታዊ የኢኮኒሚ ትብብር አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረውና በቤጂንግ በተካሄደው የቻይና-አፍሪካ ትብብር ፎረም (FOCAC) የተመዘገቡ ስምምነቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.