Fana: At a Speed of Life!

4 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ይከናወናል

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት በ4 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፋኖሴ መኮንን እንዳሉት ÷ የአፈር ለምነትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የአካባቢ ሥነ ምሕዳርን ከመጠበቅ ባለፈ የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተከናወነ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ33 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት እንዲያገግም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

ዘንድሮ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ፋኖሴ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በሁሉም ክልሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው ከ22 ሺህ በላይ ተፋሰሶች መለየታቸውን ነው የገለጹት፡፡

ለተፋሰስ ልማት ሥራ የሚውሉ የቁፋሮና ሌሎች መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው ÷ ለግብርና ባለሙያዎችና ቀያሾች በቂ ሥልጠና መሰጠቱን አመልክተዋል፡፡

አቶ ፋኖሴ በቀጣዮቹ ቀናት በሚጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ንቅናቄ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.