ሀገራዊ ምርጫው የተሳካ እንዲሆን የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሚና የላቀ ነው – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሚና የላቀ ነው አሉ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ የ6 ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የዋና ጽ/ቤትና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አመራሮች በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ተምሳሌታዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሚና የላቀ ነው።
ኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሒደት ሽግግር ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው ÷ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲፀና ትልቁን ሚና ስለሚጫወት ብልፅግና ፓርቲ ለቀጣይ ሀገራዊ ምርጫ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ምርጫው መላው ዓለም ተምሳሌት የሚያደርገው እንዲሆን ለማድረግ ጠንካራ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራዎች እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ያስቻሉ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡
ለአብነትም ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ገዢ ትርክትን ለማጽናትና ወንድማማችነትን (እህትማማችነትን) የሚያጎለብቱ በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ዘርፉ ባለፉት 6 ወራት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎች ፓርቲው በተለያዩ መስኮች ያሳካቸውን ድሎች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ድርሻ ማበርከቱን ጠቅሰው÷ በዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራዎችን በተጠናከረ መንገድ በመስራት ፓርቲው በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቀጣናውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ በመፍጠር ተምሳሌታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ማሳየት መቻሉን ተናግረዋል።