በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው አለ።
የቢሮው አማካሪ አቶ ሽቤ ክንዴ እንዳሉት፤ የተገኙ ተሞክሮዎችን በማስፋት በዚህ ዓመት በስምንት ዋና ዋና ከተሞች እና በ20 መካከለኛና አነስተኛ ከተሞች የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
እስካሁን ከ24 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድን ጨምሮ የእግረኛ፣ የብስክሌትና ሌሎችን መሰረተ ልማቶችን ያካተተ የኮሪደር ልማት ተከናውኗል ብለዋል።
ልማቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ የህፃናት መጫዎቻ፣ አደባባዮችና ሌሎች የመዝናኛ ስፍራዎችን አካትቶ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ለልማት ስራው ከ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብሩ ከህብረተሰቡ በድጋፍ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል።
በልማት ሥራው አንድ ሚሊየን ለሚጠጉ ወገኖችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው ቀደም ሲል በልማት ወደኋላ ቀርተው የነበሩ ከተሞችን ደረጃቸውን በጠበቀ አግባብ እንዲገነቡ ማስቻሉን መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ለአረንጓዴ ቦታና ለመዝናኛ ስፍራ ትኩረት ሰጥቶ እየተከናወነ በመሆኑ የከተሞች ገጽታ እየተቀየረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ፣ ለኑሮ የተመቹ እንዲሆኑ እንዲሁም የቱሪዝም ሳቢነታቸውን በማሳደግ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው በጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተመራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ልማቱ የህብረተሰቡን የሥራ ባህል በማዳበር ኑሮውን በማሻሻል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት በሰባት ከተሞች 35 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ማከናወን እንደተቻለ አቶ ሽቤ አስታውሰዋል።