Fana: At a Speed of Life!

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ የአይችሉም ስብራቶችን የጠገነችበት ነው – እናትዓለም መለሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ የአይችሉም ስብራቶችን የጠገነችበት ነው አሉ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ እናትዓለም መለሰ፡፡

ይህንን የገለጹት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ እንደ ሀገር የተከናወኑ ስራዎችና የተመዘገቡ ስኬቶችን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።

በስድስት ወሩ በተለያዩ ዘርፎች ሰፋፊ የልማት ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ የማንሰራራት ዓመት ብላ በጀመረችው መሠረት ይህንን የሚያረጋግጡ ስኬቶችን እያስመዘገበች መሆኗን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት በ30 ቢሊየን ዶላር ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ማብሰራቸውን በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡

ከነዚህ መካከል ባሳለፍነው ቅዳሜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታው የተጀመረው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የኢትዮጵያንና አፍሪካን የአይችሉም ስብራቶች የጠገነና የኢትዮጵያ ርዕይ የተገለጠበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ያሳየና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የኢትዮጵያን ከፍታ ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተጀመሩ ሌሎች ፕሮጀክቶችም ኢትዮጵያ የያዘችውን ህልም ለማሳካት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸው፥ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና በሌሎችም መስኮች በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አመላክተዋል።

በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፥ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ተቀባይነቷና ተደማጭነቷ እያደገ መምጣቱ የተመላከተበት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.