ባህላዊ እሴቶች ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጉላት እየተሰራ ነው – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደሬሽን ም/ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ባህላዊ እሴቶች የወል እውነቶችና የብሔራዊ ትርክቶች መሠረት በመሆናቸው ለሀገር ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማጉላት እየተሰራ ነው አሉ።
የቤንች ዘመን መለወጫ በዓል “ቢስት ባር” በዛሬው ዕለት በሚዛን አማን ከተማ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ያሏትን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ወደ ጥቅም በመቀየር ለዘላቂ ብልጽግና መስፈንጠሪያ እንዲሆኑ መስራት ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ የብዝኃ ባህሎች ማዕከልና የመቻቻል ማሳያ የሆነች ታላቅ ሀገር ናት ያሉት አፈ ጉባኤው፥ ለከፋፋይና ነጣጣይ ትርክት የማይመቹ ሕዝቦች መገኛ መሆኗን አውስተዋል፡፡
የብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች የወል እውነቶችና የብሔራዊ ትርክቶች መሠረት መሆናቸውን ገልጸው፥ ለሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ጎልቶ እንዲወጣ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ቢስት ባር” የደረሰን እህል ተከፋፍሎ በመቃመስ ወደ አዲስ ዓመት የሚሸጋገሩበት፣ ምስጋና የሚቀርብበትና የይቅርታ በዓል መሆኑን አውስተዋል።
ከዚህም ባሻገር የበዓሉ ሰላም የማጽናት እሴት ከክልሉ አልፎ ለሀገር እንደሚጠቅም ነው የገለጹት፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ቱባ ባህሎችን ወደ አደባባይ በማውጣት የጥንታዊ አባቶቻችንን ጥበብና ፍልስፍና ለልማታችን ተደማሪ አቅም ለማድረግ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።
ያለ ልዩነት የሚከበረው የቢስት ባር በዓል ለህዝቦች አብሮነት መጠናከር ያለውን ከፍተኛ ፋይዳ በአግባቡ ለመጠቀም ይዘቱን ሳይቀይር ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡