Fana: At a Speed of Life!

የኢንዱስትሪ ማዕከሉ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶጃት የኢንዱስትሪ ማዕከል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡

አቶ አደም ፋራህ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ከሚካሄደው የብልፅግና ፓርቲ የስድስት ወራት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ አስቀድሞ በዛሬው ዕለት በክልሉ ስልጤ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

የመተባበርና የመደጋገፍ ድልብ ባህል ባለቤትና የሥራ ወዳድነት ተምሳሌት በሆነው ስልጤ ዞን በመገኘት የተመለከትናቸው ሰፋፊ የልማት እንቅስቃሴዎች የብልፅግና ጉዟችንን ፍጥነት በተጨባጭ የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

በጉብኝታቸውም በዞኑ ወራቤ ከተማ በመንግስትና በባለሀብቶች ቅንጅት በ11 ሺህ ሄክታር ላይ በፍጥነት እየለማ የሚገኘውን የሶጃት (ንጋት) የኢንዱስትሪ ማዕከል ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ማዕከሉ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸው፥ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ በምናደርገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን አይተናል ብለዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ በ9 ሄክታር መሬት ላይ የስልጤን ድንቅ ባህል ከዘመናዊነት ጋር አጣምሮ እየለማ ያለው የወንዝ ዳርቻ ከተማዋን ይበልጥ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

በአቶት የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ፕሮጀክት ባደረግነው ምልከታ የሌማት ትሩፋት እሳቤ ወደ ግል ዘርፉም እየተስፋፋና ውጤት እያመጣ መሆኑን አይተናል ነው ያሉት፡፡

ወደ ሁሉም አካባቢዎች እየየስፋፋ የሚገኘው የገጠር ኮሪደር ልማት የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወትና የአካባቢዎቹን ገጽታ እየቀየረ መሆኑን በተግባር አይተናል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.