የብልጽግና ፓርቲ የ6 ወራት አፈጻጸም ግምገማ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን (ዶ/ር) ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የፓርቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አቶ አደም ፋራህ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት÷ መድረኩ ፓርቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ በዋና ዋና የፓርቲ ስራዎች ያከናወናቸውን ተግባራት ይገመግማል፡፡
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን መድረኩ በፓርቲው ሚናዎች ላይ በስፋት ይመክራልም ነው ያሉት።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ቢሆነውም በልማት ተምሳሌት መሆን ችሏል ያሉት አቶ አደም÷ ለዚህም የፓርቲው የአመራር ቁርጠኝነትና የሕዝብ ተሳትፎ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል፡፡
እንደሻው ጣሰው (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገ ርብርብ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የአመራሮች ቡድን ሆሳዕና ከተማ ከሚካሄደው የፓርቲው የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አስቀድሞ በትናንትናው ዕለት በክልሉ ምስራቅ ጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡
በዚህም አመራሮቹ በቡታጅራ ከተማ የአቮካዶ ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት፣ ቀሸት ንብ ማነብ ስራ ማህበር እና ደስታ ጋርመንትን ምልከታ አድርገዋል።
እንዲሁም በወራቤ ከተማ በመንግሥትና በባለሀብቶች ቅንጅት በ1 ሺህ ሄክታር ላይ በፍጥነት እየለማ የሚገኘውን የሶጃት (ንጋት) የኢንዱስትሪ ማዕከል ያለበትን ደረጃ መመልከታቸው ይታወሳል።