ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና ተሰጠው
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደመቀና የሀገር ገፅታን በሚገነባ መልኩ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረገው አስተዋፅኦ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እውቅና ተሰጠው፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ባካሄደው የእውቅና መርሐ ግብር ላይ በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ልዩ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
በዚህም መሰረት ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በዓሉ በደመቀና የሀገር ገፅታን በሚገነባ መልኩ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ላደረገው አስተዋፅኦ እውቅና ተሰጥቶታል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ መገናኛ ብዙሃን በዓሉን ለማድመቅና በበዓሉ የሀገርን ገፅታ ለማሳየት የተወጡትን ሚና አድንቀዋል፡፡
የፋና የሬዲዮ ጣቢያዎች ስራ አስፈፃሚ ትዕግሥት ስለሺ በበኩላቸው÷ እውቅናው ፋና በህብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር፣ በጋራ ትርክት ግንባታ፣ በሀገር ገፅታና በህዝቦች ትስስር መጠናከር ላይ ለሚሰራው ስራ ተጨማሪ አቅም የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
በማርታ ጌታቸው