የኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ግሽበት ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የዋጋ ግሽበት በ2012 ከነበረበት 30 በመቶ በታህሳስ ወር 2018 ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል አሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እምርታ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ ባለፉት የሪፎርም ዓመታት የገንዘብ ፖሊሲን የማዘመን፣ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን የማሻሻል፣ የፋይናንስ ዘርፍ ለውጥና የተቋማዊ ማሻሻያን ጨምሮ ዋና ዋና ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
እነዚህ የማሻሻያ ተግባራት የዋጋ ግሽበትን በሰኔ 2012 ከነበረበት ከ30 በመቶ በታህሳስ 2018 ላይ ወደ 9 ነጥብ 7 በመቶ ለመቀነስ አስችለዋል ነው ያሉት፡፡
በውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ትግበራ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ ባለፈ በህጋዊና ትይዩ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በዚህም አሁን ላይ ለግሉ ዘርፍ የሚቀርብ የብድር ድርሻ 77 በመቶ ደርሷል ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥው÷ የዲጂታል አካውንቶችን 254 ሚሊየን ማድረስ መቻሉንም አስገንዝበዋል፡፡
የዋጋ ንረትን በነጠላ አሃዝ እንዲቆይ ማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ገበያውን የበለጠ ተገማችና የተረጋጋ ማድረግ፣ የባንኮች ውህደትና ግዢን ተግባራዊ ማድረግ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራ ተቋምን ማደራጀት፣ የወለድ ነጻ የባንክ ስርዓትን ማጠናከር ሌሎች ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡