Fana: At a Speed of Life!

 ተበታትኖ የቆየውን ሀብት በተደራጀ መንገድ የማስተዳደር ስራ ተግባራዊ እየሆነ ነው – ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ተበታትኖ የቆየውን ሃብት በተደራጀ መንገድ የማስተዳደር ስራ ተግባራዊ እየሆነ ነው አሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፡፡

‌‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እመርታ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ 41 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደ አንድ በመሰብሰብ በ2014 ዓ.ም መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡

ተቋሙ ከመመስረቱ አስቀድሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ፣ የኦዲት፣የካፒታል፣ የብድር ጫናና የኮርፖሬት አስተዳደር ችግር ውስጥ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ዘመናዊ የባለቤትነት፣ የአስተዳደር ስርዓትና ዓለም አቀፍ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓት የተዘረጋላቸውና ዘመናዊ የኦዲት ስርዓት የሚከተሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ተቋማቱ ከኪሳራ ወጥተው ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገሩ አስችሏል ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ባለፉት አራት ዓመታት የተቋማቱ አጠቃላይ ገቢ ቀድሞ ከነበረበት ከ704 ቢሊየን ብር ወደ 6 ነጥብ 1 ትሪሊየን ብር ማደጉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያን ሃብት የማወቅ፣ ተበታትኖ የቆየውን ሃብት በተደራጀ መንገድ የማስተዳደር ስራ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዛሬ ላይ በ36 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ በአጠቃላይ በእነዚህ ተቋማት ስር ያለው የሃብት መጠንም 8 ነጥብ 2 ትሪሊየን ብር መደረሱን ተናግረዋል፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን አበርክቶ ይበልጥ በማጠናከር ከኢትዮጵያ ተሻግረው በአፍሪካ ገበያ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.