ባለስልጣኑ በካፒታል ፈላጊዎችና ካፒታል አቅራቢዎች መካከል ድልድይ የሚሆን ስርዓት እየገነባ ነው – ሃና ተኽልቁ
አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የካፒታል ገበያ ስርዓት ፈጠራን በማበረታታት በካፒታል ፈላጊዎችና ካፒታል አቅራቢዎች መካከል ድልድይ የሚሆን ስርዓት እየገነባ ነው አሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኽልቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የመንግሥት ፋይናንስና ሌሎች የፋይናንስ ዘርፍ ተቋማትን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የፋይናንስ እመርታ ኮንፈረንስ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በ2011 ዓ.ም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለመጀመሪያ ጊዜ ከተዋወቀ ወዲህ የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣንን፣ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ገበያ እና የማዕከላዊ ሰነደ ሙዓለንዋዮች ግምጃ ቤትን መፍጠር ተችሏል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃና ተኽልቁ እንዳሉት፥ እነዚህን ተቋማት በማቋቋም የካፒታል ገበያ አገልግሎት የሚሰጡ 15 ተቋማት ፈቃድ አግኝተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡
ተቋማቱ የተከፈለ ካፒታላቸው 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መድረሱን ጠቁመው፥ በተጨማሪም 10 ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለንዋይ ገበያ ላይ ለመመዝገብ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በባንኮች መካከል በገበያ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ልውውጥ እያደገ መጥቷል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፥ በቀጣይ ዘርፉ ኢኖቬሽንና ስራ ፈጠራን በመደገፍ ለሀገራዊ እድገቱ የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።