Fana: At a Speed of Life!

የገበታ ቱሪዝም…

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመሩ የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ በመሰረታዊነት እየቀየሩ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከአንድ ድንጋይ ከተጠረቡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጀምሮ እስከ ጥያ ትክል ድንጋይ፣ ከሶፍ ዑመር ዋሻ እስከ ጎንደር አብያተ መንግስታት፣ ከአክሱም ሐውልት እስከ ሐረር ግንብ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ናት።

በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበች ሲሆን፥ በተለይ የጥምቀት፣ የመስቀል፣ የፊቼ ጫምበላላ በዓላትንና የገዳ ስርዓትን ጨምሮ እነዚህ ቅርሶቿ አጓጊ የጉዞ መዳረሻና ተመራጭ የተሪዝም መናኸሪያ እንድትሆን ረድተዋል።

እነዚህ አቅሞች የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማሳደግና ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ መልከዓ ምድሮችና ህያው ባህሏ የጉዞ መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትቀጥል ከለውጡ ወዲህ በቱሪዝም መሠረተ ልማት እየታደሰች ነው፡፡

እጅግ ያማሩና የየራሳቸውን አካባቢዎችና በድምር የሀገር ገጽታን እየቀየሩ ያሉ ሪዞርቶችን በማልማት ተደብቀው የነበሩ እምቅ የመስህብ ስፍራዎችን፣ መልከዓ ምድሮችን፣ ፓርኮችንና ታሪካዊ ቦታዎችን እየገለጠች ትገኛለች።

በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጸነሰው የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ በመሠረታዊነት እየቀየሩ ይገኛሉ።

በገበታ ለሀገር ኢኒሼቲቭ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ጎርጎራ፣ ሀላላ ኬላ፣ ጨበራ ጩርጩራና ወንጪ ፕሮጀክቶች ለአካባቢዎቹ ተደማሪ የቱሪዝም አቅምን ፈጥረዋል፡፡

በመቀጠልም ሰባት የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የተጀመሩ ሲሆን እነዚህም ሌሎች ክልሎችን ጨምሮ በትግራይ፣ በሶማሊ፣ አፋርና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩት ይገኙበታል።

እነዚህ ኢንሼቲቮች ከቢሮ ወደ ከተማ፣ ከከተማ ወደ ሀገር እየሰፉ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች፣ መልከዓ ምድራዊ ውበቶችና ፓርኮችን በመሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር አዳዲስ የቱሪዝም እድሎችን እንዲከፈቱ መደላድል እየፈጠሩ ነው።

በመሠረተ ልማት እጦት ከተጓዦች ተደብቀው የቆዩ መንፈስን የሚያድሱ የመስህብ ስፍራዎች፣ መልከዓ ምድሮች፣ እጅግ የተለዩ አዕዋፋትና ዕጽዋቶች ለጎብኝዎችና አሳሾች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የተሻሻለ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ለጎብኚዎች ተደራሽነትና ደህንነትን የሚያበረታታ ሲሆን፥ የጎብኚዎችን የኢትዮጵያ ቆይታና ጉብኝት ቀላል እንዲሆን ለማስቻል የመንገድ መሠረተ ልማትና የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ለማሻሻል ሰፋፊ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ከዚህ አንፃር በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያዎች፣ በመዲናዋና በሁሉም ክልሎች የተሰሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ለዚህ አንፀባራቂ ምሳሌ ናቸው።

በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ ግድቦችና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ለቱሪዝም መዳረሻ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘላቂ ኃይል ለማቅረብ  የሚያግዙ ናቸው።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.