ቼልሲ ተጋጣሚውን ሲያሸንፍ ሊቨርፑል አቻ ተለያየ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ22ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ቼልሲ ተጋጣሚውን ሲያሸንፍ ሊቨርፑል አቻ ተለያይቷል።
12 ሰዓት ላይ በተጀመረው የቼልሲ እና ብሬንትፎርድ ጨዋታ ቼልሲ 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።
በጨዋታው የቼልሲን ማሸነፊያ ግቦች ጃኦ ፔድሮ በጨዋታ ኮል ፓልመር በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ አሳርፈዋል።
እንዲሁም በተመሳሳይ ሰዓት በአንፊልድ ሮድ በተካሄደው ጨዋታ በርንሌይን ያስተናገዱት ሊቨርፑሎች 1 ለ 1 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።
በጨዋታው የሊቨርፑልን ብቸኛ ግብ ፍሎሪያን ቪርትዝ ሲያስቆጥር ዶሚኒክ ሶቦዝላይ ፍጹም ቅጣት ምት አምክኗል፤ የበርንሌይን የአቻነት ግብ ማርከስ ኤድዋርድ ከመረብ አሳርፏል።
በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ ጨዋታዎች አዲስ አዳጊው ክለብ ሰንደርላንድ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ሊድስ ዩናይትድ ፉልሀምን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ቀደም ብሎ ማንቼስተር ዩናይትድ እና ማንቼስተር ሲቲ ያደረጉት ጨዋታ በዩናይትዶች 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
እንዲሁም ዌስትሀም ዩናይትድ ቶተንሀምን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ የማሸነፊያ ግቦቹን ክሪሰንሲዮ ሰመርቪል እና ካሉም ዊልሰን አስቆጥረዋል።
የቶተንሀምን ብቸኛ ግብ ደግሞ ክሪስቲያን ሮሜሮ ከመረብ አሳርፏል።
የሊጉ ጨዋታ ቀጥሎ ሲካሄድ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከኖቲንግሃም ፎረስት የሚያደርገው ጨዋታ ምሽት 2፡30 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።