Fana: At a Speed of Life!

ዛሬ ያለንን ጥንካሬ ለትውልድ በሚተርፍ መንገድ የኢትዮጵያን ሃብቶች መግለጥ ይኖርብናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ያለንን ጉልበትና ጥንካሬ ለመጪዎቹ ተከታታይ ትውልዶች በሚተርፍ መንገድ የኢትዮጵያን ሃብቶች መግለጥና መቀጠል ይኖርብናል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የገበታ ለትውልድ ሥራ የመጀመሪያው መዳረሻ የሆነውን ደንቢ ኢኮ ሎጅን በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል።

ይህንን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመደመር ሀሳብ መንግሥትን፣ የግል ዘርፉን፣ ተፈጥሮን እና የትናንትን ወረት ለነጋችን ብሩኅነት በአንድ ያሰባስባል ብለዋል።

በዚህም ዛሬ ጠዋት በተመረቀው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ይኽን በግልጽ መመልከት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሥራው ከአካባቢው በተገኙ የግንባታ ቁሳቁሶች እና በአካባቢ አቅም የተገነባ በመሆኑ ዘላቂነትን እና ባለቤትነትን ያንፀባርቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሀገራችን በባሕል፣ በተፈጥሮ እና ታሪካዊ ጥሪቶች የታደለች በመሆኗ ዛሬ ያለንን ጉልበት እና ጥንካሬ ለመጪዎቹ ተከታታይ ትውልዶች በሚተርፍ መንገድ ሀብቶቿን መግለጥ መቀጠል ይኖርብናል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.