Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሌላት ውበት፣ ጸጋና ሃብት የለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እኛ ነን ማስተዋል ያቃተን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ውበት፣ ጸጋ እና ሃብት የለም አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገበታ ለትውልድ ሥራ የመጀመሪያው መዳረሻ የሆነውን ደንቢ ኢኮ ሎጅን በዛሬው ዕለት በይፋ መርቀዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ብዙ ሰው ሀገሩን ጠንቅቆ ሳያውቅ፣ በሀገሩ ያለን ውበትና ጸጋ ማየት ሳይችል ወጣ ሲል የሰው የሚያደንቅበት ሁኔታ እንዳለ አንስተዋል።
ደንቢ ኢኮ ሎጅን መጥተው ማየት ቢችሉ ከዓለም ልዩ እና ምርጥ ቦታዎች መካከል ለመሆን ብቁ መሆኑን ያምናሉ ብለዋል።
ኢኮ ሎጁ ወደ ሚገኝበት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ወረዳ መጓዝ ከዚህ ቀደም አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ሰዎች በቀላሉ በአውሮፕላን ተጉዘው የኢኮ ሎጁን አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ማንኛውም ሰው እዚህ ቦታ መጥቶ ከቤተሰቡ ጋር ቢያሳልፍ ዘመኑን ሙሉ የተመኘውን ገነት በጨረፍታ የሚያይበት ይሆናል ነው ያሉት።
መደመር ለሚዛን አማን፣ ለቤንች፣ ለሸኮ ፈጣሪ የሰጠውን ሀብት በሚገባ አስውቦ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ይህን ስፍራ እኛ አልሰራነውም አብዛኛው ነገር የፈጣሪ የእጅ ስራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፈጣሪ የሰጠንን ውበት ብቻ ወስደን ዝም ካልን አሁን የታየውን ውበት ማየት አንችልም ሲሉም አብራርተዋል።
የደርግ መንግሥት ዜጎች በማስተባበር በሺህ የሚቆጠር ሄክታር ጫካን ወደ ገንዘብ በመቀየር ቡና ተከለ፣ ግድብም በመገደብም የሃይል ማምረቻ ሰራ በማለት አስታውሰው፤ አሁን ያለውን ውበት ለማምጣት ግን በቂ እንዳልነበር አስረድተዋል።
አሁን ጊዜው ተለውጦ በመንግሥት እና ባለሃብት፣ በመንግሥት እና ሕዝብ ትብብር መስራት ሲጀመር ይህንን የመሰለ ሀብት እና ውበት ተገልጧል ነው ያሉት።
ኢኮ ሎጁ ውሃውን፣ ቡናውን እና ጫካውን የሚተካ ሳይሆን የእነሱን ውበት የሚያጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ሀገራቸውን ለሚወዱ እና መጎብኘት ለሚፈልጉ ሁሉ የሎጁ መገንባት ወሳኝ በመሆኑ በቅርብ ሆነ በሩቅ ያሉ ሁሉ እንዲጎበኙት ግብዣ አቅርበዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ በኑሮ ድሃ ቢመስልም ልቡ ሃብታም እንደሆነ ጠቅሰው፤ የአካባቢው ማህበረሰቦች ደግ፣ እንግዳ ተቀባዮች እና የተፈጥሮ ባለ አደራዎች ናቸው በማለት ገልጸዋቸዋል።
ሁለንተናው የተሟላ በሰው እጅ ሊሰራ የማይችል በስዕል ብቻ የሚገለጥ ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብሎ ለማመን ቢያስቸግርም እውነታው ግን እኛ ነን ማስተዋል ያቃተን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ የሌለ ውበት፣ ጸጋ እና ሃብት የለም ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንዲህ አይነት ሃብት ዐይን ካልተገለጠ ቢቀመጥም ልክ ከአፈር ውስጥ እንደተቀመጠ ወርቅ ማለት ነው ብለዋል።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.