Fana: At a Speed of Life!

የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ – ቲከሻ ቤንጊ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸኮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ቲከሻ ቤንጊ” የምስጋና በዓል ነው።

“ቲከሻ” የሚለው ቃል ትርጓሜው ምስጋና ሲሆን “ቤንጊ” የሚለው ቃል ደግሞ በዓል የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል።

ቲከሻ ቤንጊ የሸኮ ህዝቦች አዝመራውን ከንፋስ እና በረዶ እንዲሁም ከዋግ በሽታ ጠብቆ ላቆየላቸው ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ለዘመናት ያዳበሩት ድንቅ የባህል እሴት ነው።

ሸኮዎች ቲከሻ ቤንጊን የሚያከብሩት ቡናና ቅመማቅመም እንዲሁም የደረሰውን እህል ሰብስበው ወደ ጎተራ በሚያስገቡበት በጥር ወር ነው።

የብሔረሰቡ ባህል አዋቂ የሆኑት አቶ ከርካስ ኡፋ እንደሚሉት፥ እህል ከተሰበሰበ በኋላ ሸኮዎች የጎሳ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት እህሉን ጠብቆ ላደረሰ ፈጣሪ ምስጋናን በማቅረብ ወደ አዲስ የዘመን ምዕራፍ መሻገራቸውን ያበስራሉ፡፡

ከበሽታና ከቸነፈር ተጠብቀው ደስታ ወደሞላበት የአዝመራ ወቅት ወይም አዲስ ምዕራፍ በመሻገራቸው ምስጋና የሚያቀርቡ ሲሆን፥ ታላላቅ አባቶች መጪው ጊዜ ያማረ ሆኖ እንዲቀጥል ይመርቃሉ።

በአዲሱ ዘመን የሚመጣን ችግር ፈጣሪ እንዲመልስ፣ ልጆች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ የተወለዱት እንዲያድጉ፣ የተዘራው እህል ፍሬ እንዲያፈራና አጠቃላይ ምድሪቱ ሁሉ ሰላም እንድትሆን ሸኮዎች ምኞታቸውን ይገልጻሉ።

ሸኮዎች ቲከሻ ቤንጊ በዓል መከበር ካቆመ ከ50 ዓመት በኋላ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እያከበሩ ይገኛሉ።

የቲከሻ ባህላዊ እሴቶች ለሠላምና አብሮነት ከፍ ያለ አበርክቶ ያላቸው በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ባህል ጠብቆ ማቆየትና እሴቶቹን መተግበር አለበት ሲሉ የሀገር ሽማግሌዎች አስገንዝበዋል።

በተስፋዬ ምሬሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.