የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 4 ሺህ 158 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ላከ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የልማት ሥራዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
አቶ አሻድሊ ሀሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በኮሪደር ልማት፣ ትምህርት፣ ሰላም፣ ጤና፣ ንግድ፣ ግብርና፣ በገቢ አሰባሰብ እና ሌሎች ዘርፎች ባለፉት 6 ወራት የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው÷ በተለይም የወርቅ ምርትን ውጤታማነት ለማሳደግ በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በክልሉ 3 ሺህ 525 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለመላክ ታቅዶ 4 ሺህ 158 ኪሎ ግራም ወርቅ መላክ መቻሉን ተናግረዋል፡
አቶ አሻድሊ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ንግድ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ኮሚቴ ተዋቅሮ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን በማጠናከር ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እና የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ አፈጻጸምን ይበልጥ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡንም አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ