Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረች

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏል አለ የጤና ሚኒስቴር፡፡

የኢትዮጵያ ድንገተኛ የማሕበረሰብ ጤና አደጋ ፈጣን ምላሽና አመራር ስኬቶች እንዲሁም የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ቁጥጥር ማብሰሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በመርሐ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እና አጋር አካላት ተገኝተዋል፡፡

ዶ/ር መቅደስ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መከላከልና አክሞ ማዳንን መሰረት በማድረግ የዜጎችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው፡፡

ለወረርሽኝ የማይበገር ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለመገንባት በትኩረት መሰራቱን ጠቁመው÷ በዚህም ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል፡፡

ለአብነትም በቅርቡ በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ነው ሚኒስትሯ ያበሰሩት፡፡

ይህ ስኬት እንዲገኝ ከፊት ሆነው ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ የማርበርግ ቫይረስን በመዋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎች ምስጋና ቀርቧል፡፡

ዶ/ር መቅደስ ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነውን እና ያልተለመደውን የማርበርግ ቫይረስ መቆጣጠር በመቻሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

ስኬቱ በሀገራች ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጉምና አሻራ አለው ያሉት ሚኒስትሯ÷ በሽታውን ለመቆጣጠር ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.