1 ሺህ 800 ሰዎችን በማዘዋወር ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ከግል ተበዳዮች አሰባስበዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 1 ሺህ 800 ሰዎችን በማዘዋወር ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ከግል ተበዳዮች አሰባስበዋል የተባሉ 28 ግለሰቦች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ እንዳስረዳው፤ ክሱን ያቀረበው በሊቢያ መስመር በሰዉ ልጅ የሚነግዱ ዋና ዋና አዘዋዋሪዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ በተካሄደ ምርመራ መነሻነት ነው።
በዚህም ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀፅ (3) እና 4 (2)፣ (ሀ)፣ (ሐ) እና (መ) ስር የተደነገገዉን በመተላለፍ በከባድ የሰዉ ልጅ መነገድ ወንጀል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 (በአዋጅ ቁጥር 1387/2017 እንደተሻሻለዉ) አንቀጽ 29 (2) ከሀ እስከ ሠ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር ቁጥር 1159/2011 አንቀፅ 3 (1) እና 65 (1) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ህገ ወጥ ሃዋላ በመስራት ሃብት የማሸሽ ወንጀል ክስ አቅርቧል፡፡
ተከሳሾቹ በሰዉ ልጅ ለመነገድ በማሰብ የተደራጀ የወንጀል ቡድን በማደራጀት እንዲሁም የቡድኑ አመራር እና አባላት በመሆን ወንጀል ድርጊቱ ላይ መሳተፋቸውን አስረድቷል።
ተከሳሾቹ ወንጀሉን ለመፈጸም የወንጀል ቡድን አደራጅተው በስራቸዉ ሌሎች አነስተኛ ስራ የሚሰሩ ደላሎችን በመመልመል ሰዎች በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ገብተዉ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ በማሳመን ወደ ባህርዳር እና ጎንደር ከተሞች ሲልኩ መቆየታቸውን አብራርቷል።
እንዲሁም ከባህርዳር እና ጎንደር አካባቢ ሰዎችን ወደ ሱዳን ድንበር የሚያጓጉዙ ተቀጣሪዎችን በማዘጋጀት ኢመደበኛ በሆነ መንገድ ሰዎችን ከሀገር ሲያስወጡ ቆይተዋል ነው ያለው።
ሰዎቹ ከኢትዮጵያ ድንበር ከወጡ በኋላ በዘረጉት የወንጀል መረብ አማካኝነት ወደ ሊቢያ ወስደው በመጋዘኖች ሲያጉሩና በሊቢያ በሚገኙ ተከሳሾች እና ግብረአበሮቻቸዉ በሚያስተዳድሩት መጋዘኖች ውስጥ በህይወት ለመቆየት ብቻ የሚበቃቸዉን ምግብ እንዲያገኙ አድርገዉ በመያዝ እንዲሁም ወደቤተሰቦቻቸዉ ስልክ በመደወል ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ ገንዘቡ እስኪከፈል በእዳ መያዣ ማድረጋቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል።
በፍጥነት ገንዘብ ለመክፈል ላልቻለ የተበዳይ ቤተሰቦች ተበዳዮችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየደበደቡ እና እያሰቃዩ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረፅ ወደቤተሰቦቻቸው በመላክ ገንዘብ እንዲከፈል ጫና ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ገልጿል።
የተበዳይ ቤተሰቦች ገንዘብ አፈላልገዉ ለመክፈል ፍቃደኛ ሲሆኑ ስምንት ተከሳሾች እና ሌሎች ግብረአበሮቻቸውን የባንክ ሂሳብ በመጠቀምና ገንዘብ ሲሰበስቡ ቆይቷል ብሏል።
ተይዘዉ በተከሰሱት ስምንት ገንዘብ ሰብሳቢዎች አማካኝነት ብቻ ብር 2 ቢሊየን 160 ሚሊየን 863 ሺህ 361 ብር መሰብሰባቸውን የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያሳያል፡፡
ተከሳሾች የሰበሰቡትን ገንዘብ በፍጥነት በመቀባበል እና በማስተዳደር ከገንዘቡ ሲጠቀሙ እና ለግብረአበሮቻቸዉ ክፍያ መፈጸማቸውን አመላክቷል።
ተከሳሾቹ ከዝውውር ወጪ የተረፈ ቀሪ ገንዘብን ከሀገር እንዲሸሽ በማድረግ በውጪ ሀገር ሃብት አፍርተውበት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ማፍራታቸውንም ጠቅሷል።
በአጠቃላይ በተደረገው ምርመራ በተከሳሾች በጠቅላላ 1 ሺህ 800 ሰዉ የተጓጓዘ ሲሆን የ85 ሰዎች ማንነት መለየቱን አቃቤ ህግ አስረድቷል።
ከ85ቱ መካከል የሁለት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን፣ ሁለት ሰዎች በድብደባ ምክንያት ለበሽታ መዳረጋቸውን እና 15 ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።
በሲፈን መኮንን