Fana: At a Speed of Life!

በኖርዊች ሲቲ ድንቅ ብቃቱን እያስመለከተ የሚገኘው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሊ አህመድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከካናዳው ቫንኩቨር ኋይትካፕ የእንግሊዙን ኖርዊች ሲቲ በጥር የዝውውር መስኮት የተቀላቀለው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አሊ አህመድ በርካቶችን በብቃቱ እያስደመመ ይገኛል፡፡

አሊ አህመድ በፈረንጆቹ 2000 በካናዳ ቶሮንቶ የተወለደ ሲሆን ወላጆቹ ከ30 ዓመታት በፊት ከሐረርጌ ወደ ካናዳ በማቅናት ኑሯቸውን በዚያው አድርገዋል።

የእግር ኳስ ህይወቱን በቶሮንቶ እግር ኳስ ክለብ አካዳሚ የጀመረው አሊ፤ ከሜጀር ሊግ ሶከሩ ቫንኩቨር ኋይትካፕ ወደ እንግሊዙ የሻምፒዮን ሺፕ ተሳታፊ ኖርዊች ሲቲ በጥር የዝውውር መስኮት በሁለት ሚሊየን ፓውንድ በመቀላቀል ደረጃውን ከፍ አድርጓል፡፡

ኖርዊች ሲቲ የሻምፒየን ሺፑን መሪ ኮቨንተሪን ሲያሸንፍ አንድ ግብ በማስቆጠርና ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ በማቀበል የጨዋታው ኮከብ በመሆን አድናቆትን ተጎናጽፏል፡፡

ከሶስት ሳምንታት በፊት ከቫንኩቨር ኋይትካፕ ኖርዊች ሲትን የተቀላቀለው የ25 ዓመቱ ተጫዋች ለክለቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁለት ግብ በማስቆጠርና ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶች በማቀበል አጀማመሩን አሳምሯል፡፡

አሊ እያደረገ ያለውን ድንቅ እንቅስቃሴ ተከትሎ አስታየታቸውን እየሰጡ የሚገኙ ተንታኞች ተጫዋቹ የተሻለ ተስፋ ከፊቱ እንደሚጠብቀው ጠቁመዋል።

በሻምፒየን ሺፑ ከወራጅ ቀጠና በአራት ነጥብ ርቆ የሚገኘው ኖርዊች ሲቲ የአሊ ቡድኑን መቀላቀልን ተከትሎ ጥሩ መነቃቀት እያስመለከተ ይገኛል፡፡

በ2019/20 እንዲሁም በ2021/22 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበረው ኖርዊች ወደ ሊጉ ለማደግ በሚያደርገው ጉዞ የአሊ እንቅስቃሴ ይበልጥ እንደሚረዳው ተመላክቷል፡፡

ከኢትዮጵያውያን ወላጆች የተገኘው አሊ አፈንዲ አህመድ፤ ከ2023 ጀምሮ ለካናዳ ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡

በአማካኝ የሜዳ ክፍል እና በክንፍ የተዋጣለት እንቅስቃሴን በማድረግ የሚጫወተው አሊ፤ ወደፊት በትልቅ ደረጃ ሊታይ የሚችል ባለተሰጥኦ መሆኑን በርካቶች መስክረውለታል።

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.