Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ላቀፉ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ይሰጣል

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተተኪ ስፖርተኞችን ላቀፉ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ይሰጣል አለ የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፡፡
ቢሮው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን አጠቃቀም በሚመለከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የቢሮው ኃላፊ በላይ ደጀን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በከተማዋ ጥራታቸውን ጠብቀው ከተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የተስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያዎቹ በቀጣይ የሚያስፈልጋቸውን የእድሳት ወጪ ለመሸፈን እንዲችሉ የጤና ቡድኖችና ልምምድ የሚሰሩ ክለቦች በየደረጃው በክፍያ እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል።
በተለይም አዳጊና ተተኪ ስፖርተኞችን ላቀፉ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው፥ በገንዘብ መጠቀም የሚችሉና የማይችሉትን በመለየት በቀጣይ ተጠቃሚነት ላይ ተጨማሪ መመሪያ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
አቅም የሌላቸው ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በነጻ እንዲጠቀሙ ይደረጋል ያሉት ኃላፊው፥ ከከተማ አስተዳደሩ ደንብና መመሪያ ውጪ የሚሰሩ የማዘውተሪያ ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር በማድረግ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
ግንባታቸው ተጠናቅቆ ርክክብ ያልተደረገባቸውና በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት ያልጀመሩ ማዘውተሪያዎችን በአፋጣኝ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ይሰራል ነው ያሉት፡፡
ተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ፍላጎትና ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልጸው፥ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ደረጃቸውን የጠበቁ ተጨማሪ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የመገንባት ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
በእንዳልካቸው ወዳጄ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.