Fana: At a Speed of Life!

 የ90 ዓመቱ …

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የተቋማት ግንባታ አንዱ ነው። ተቋማት ትናንት የነበራቸውን ወረት በመያዝ ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ሰፊ ስራ እየተሰራ ይገኛል። በመሆኑም ከፋይናንስ እስከ ደህንነት ተቋማት ድረስ የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን እና ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተቋማት ሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውን የሚያሳዩ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል።

በዚህ የተቋም ግንባታ ሂደት ውስጥ ካለፉት መካከል ከሰሞኑ የምስረታውን 90ኛ ዓመት ያከበረው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ይጠቀሳል። አየር ኃይሉ የተቋም ግንባታ ሂደቱን በብቃት መወጣት መቻሉን የሚያሳዩ ለውጦችን ማሳየት ችሏል።

ዛሬ ለአፍሪካ ኩራት ለመሆን የበቃው አየር ኃይሉ ለደረሰበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። በ1928 ዓ.ም የተመሰረተው አየር ኃይሉ በከፍታ የተጓዘባቸው ወቅቶች የመኖራቸውን ያህልም የመፍረስ አደጋን ተጋፍጦ ያለፈበት ወቅት ነበር። በተለይም ኢትዮጵያ በጣሊያን በተወረረችበት ዘመን ህልውናው አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ከዚያ በመቀጠልም በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተከሰተውን የስርዓት ለውጥ ተከትሎ ተቋሙ ዳግም የህልውና ስጋት ላይ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር።

የአየር ኃይሉን ብቃት እና አቅም በቅርብም በሩቅም ያሉ ሲመሰክሩለት ቆይተዋል። ለአብነትም በ1960ዎቹ መጀመሪያ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አብራሪዎችን ትዕይንት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋባዥነት በክብር እንግድነት ተገኝተው የተመለከቱት የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ “የኢትዮጵያን ነጻነት ለመዳፈር የሚመጣ ይኖራል ብዬ አላምንም” ብለዋል።

ከትዕይንቱ በኋላ ምን ታዘቡ? ተብለው የተጠየቁት ኬንያታ “የኢትዮጵያን ነጻነት በሚገባ የሚጠብቅና በቂ ዋስትና ያላችሁ ለመሆኑ ይህ የአየር ላይ ትርዒት አይነተኛ ምስክር ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት።

የተመለከቱትን ትዕይንት እጅግ መገረምን የፈጠረባቸው ስለመሆኑም ምንም ሳይደብቁ ተናግረዋል።

በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ በሶማሊያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ አማካኝነት የገጠማትን ወረራ በመቀልበስ ረገድ የአየር ኃይሉ ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ታሪክ ያስታውሰዋል። በወቅቱ የጦር ጄቶች ዋነኛ እና የተለመደ ተግባር ዒላማ የተደረገ የጠላት ኃይል፣ ይዞታ እና ሎጂስቲክ ላይ ጥቃት መፈጸም ሲሆን ይህንንም በስኬት በመፈጸም ኢትዮጵያ የድል ባለቤት እንድትሆን የድርሻውን ተወጥቷል።

አየር ኃይሉ ከሚታወቅባቸው ዝናዎቹ መካከል ብቁ፣ የጠላትን አከርካሪ ሰባሪና ባለንስር ዐይን አብራሪዎችን ማምረቱ ነው። አብራሪዎቹ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳ ተልዕኳቸውን ሳያሳኩ እና ግዳጃቸውን ሳይፈጽሙ ወደ ኋላ አይሉም።

ይህ አየር ኃይል ዘመኑን የዋጀ ይሆን ዘንድ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ የማድረግ አቅሙን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሷል። ተቋሙ የደረሰበት ከፍታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጽናት ካስቀመጡት ሰፊ እሳቤ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።

በመሆኑም አየር ኃይሉ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና ልቀት ዘመኑን የዋጁ የጦር አውሮፕላኖች እና ድሮኖችን በመታጠቅ፣ የኢትዮጵያ ሰማይ አስተማማኝ ዘብ የመሆን አቅሙን አዳብሯል። በሰው ኃይል ልማት ረገድም በዕውቀት እና በሥነ-ምግባር የታነጹ ባለሙያዎች በማፍራት የላቀ የውጊያ ብቃት እና ዝግጁነት ያለው ሆኗል።

ተቋማዊ ሪፎርሙ አየር ኃይሉ ከወገንተኝነት ወጥቶ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚያገለግል በመሆን የሀገረ መንግስት ግንባታን የሚያጸና መሆኑን አረጋግጧል። የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓልም ይህንን በአግባቡ ማሳየት የቻለ ነው። አየር ኃይሉ በ90 ዓመት ጉዞው ፈተናዎችን ተሻግሮ አሁን ያለው ቁመና ብዙ መስራት የሚችል አፍላ ወጣት መሆኑን ያሳየ ነው።

በነስረዲን ኑሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.