የ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ …
አዲስ አበባ፣ ጥር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ አምስት ጨዋታዎች መደረግ ይጀምራል፡፡
ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሊጉ መሪ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
በሊጉ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው አርሰናል ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል ሁሉንም በማሸነፍ የበላይነት አለው፡፡
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል ጨዋታውን የሚያሸንፍ ከሆነ ማንቼስተር ሲቲ እሁድ እስኪጫወት ድረስ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሰባት ከፍ ማድረግ ይችላል፡፡
በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወልቭስ ከቦርንማውዝ እንዲሁም ብራይተን ከኤቨርተን ይገናኛሉ፡፡
ምሽት 2 ሰዓት 30 ላይ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡
ያለፉትን ሁለት የሊጉን ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ሁለቱ ቡድኖች ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን በሊጉ ለማሳካት የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡
የሊጉ ጨዋታ ሲቀጥል ምሽት 5 ሰዓት ላይ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ኒውካስል ዩናይትድን ያስተናግዳል፡፡
በሊጉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንዱም ድል ያላደረገው ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ፍልሚያ ተጠባቂ ነው፡፡
በሊጉ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ያልቀናው ኒውካስል ዩናይትድ በበኩሉ ወደ ድል ለመመለስ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሦስቱን ሲያሸንፍ በአንዱ ኒውካስል ዩናይትድ አሸንፎ በአንዱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡
የሊጉ ጨዋታዎች ነገ ቀጥለው ሲደረጉ ቶተንሃም ሆትስፐር ከማንቼስተር ሲቲ የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 1 ሰዓት 30 ላይ ይደረጋል፡፡
በሊጉ ከአራት ተከታታይ ጨዋታ ድል አልባ ጉዞ በኋላ በ23ኛ ሳምንት ወልቭስን በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሰው ማንቼስተር ሲቲ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡
ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በአንዱም ድል ማድረግ ያልቻለው ባለሜዳው ቡድን ቶተንሃም ሆትስፐር ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ፉክክር ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ቶተንሃም ሆትስፐር ሦስቱን ሲያሸንፍ ማንቼስተር ሲቲ ሁለቱን አሸንፏል።
ከእዚህ ጨዋታ አስቀድሞ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ከፉልሃም ጋር ይገናኛል፡፡
ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ እና አርሰናልን ያሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ለማሳካት ይፋለማል፡፡
ኖቲንግሃም ፎረስት ከክሪስታል ፓላስ እንዲሁም አስቶንቪላ ከብሬንትፎርድ በተመሳሳይ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የሚደረጉ የሊጉ የዕለቱ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
የ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ሰኞ ምሽት 5 ሰዓት ላይ ሰንደርላንድን ከበርንሌይ በማገናኘት ይጠናቀቃል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ