Fana: At a Speed of Life!

 የአገው ፈረሰኞች በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአገው ፈረሰኞች ድንቅ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

86ኛው የአገው ፈረሰኞች በዓል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተገኙበት ተከብሯል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ አስደናቂውን የአገው ፈረሰኞች ማኅበር 86ኛ ዓመት በዓል መታደማቸውንና በበዓሉ የተዘጋጀውን የፈረስ ትርዒት በእንጅባራ ከተማ መመልከታቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህ በዓል የፈረሰኞች ትርዒት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ጽናት፣ የጀግንነት ዐሻራ እና የሰላም ተምሳሌት መሆኑን አውስተዋል፡፡

ፈረስ ለኢትዮጵያ በተለይም ለአገው ሕዝብ አድራሽ፣ አራሽ፣ የድልና እና የክብር መጎናጸፊያ መሆኑን ጠቅሰው ÷ከጥንት ጀምሮ በደስታም ሆነ በሃዘን፣ በሠርግም ሆነ በጦር ግንባር ፈረስ የኢትዮጵያውያን የቅርብ ወዳጅና ታማኝ አገልጋይ ሆኖ ዘልቋል ብለዋል።

ፈረስ ከዓድዋ እስከ ጉርዓ የድልና የነጻነት አርማችን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ ዛሬ ድረስ ፈረስና የኢትዮጵያ ክብርና ነጻነት የማይነጣጠሉ፣ታሪካዊ ትሥሥራቸውም የጠበቀ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የአገው ሕዝብ እንደ አባቶቹ ጽንፈኝነትን “እምቢ” ያለ፣ ሰላምን በራሱ እጅ ያስከበረና አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማውን በፈረሱ ላይ ከፍ አድርጎ የሚያውለበልብ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

ትናንት በፈረስ ጉልበት ነጻነታችንን እንዳስከበርን ሁሉ ዛሬ ደግሞ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን የሀገራችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን ነው ያሉት።

ፈረሶቻችን ምድሩን እንዳዳረሱት ሁሉ፣ አውሮፕላኖቻችን ሰማዩን፣ መርከቦቻችን ባሕሩን፣ ምርቶቻችን ገበያውን፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ማዳረስ አለባቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ይህ የአገው ፈረሰኞች ድንቅ ባህል በዓለም ቅርስነት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው÷ በዓሉን የዓለም ቅርስ የማድረጉን ሒደት በጋራ እናሳካዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህ በዓል የአገውን ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና ሥርዓት ለዓለም የሚያሳይ “ሕያው ሙዝዬም” ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ከየገጠሩ የሚተመውሕዝብ ብዛትና ድምቀት የበዓሉን ታላቅነት እንደሚያሳይ አመልክተዋል።

አዊ ዞን ዘጠኝ ወንዞች የሚገማሸሩበት፣ ዘንገናና ጥርባ ሐይቆች የሚንፈላሰሱበት፣ ደኖችና ዋሻዎች የሞሉበት ምድር መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህን ተፈጥሯዊ ጸጋ ወደ ሀብት መቀየር ከተቻለ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የሚተርፍ ብልጽግናን እንደሚያመጣ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.