ህፃናት ከኮሮና ቫይረስ ይልቅ ትምህርት ቤት አለሜሄዳቸው ከፍ ያለ ጉዳት ያስከትልባቸዋል- የብሪታኒያ ከፍተኛ የህክምና አማካሪ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 17፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህፃናት በኮሮና ቫይረስ ተይዞው ከሚያጋጥማቸው ጉዳት ይልቅ ትምህርት ቤት አለሜሄዳቸው የሚያጋጥማቸው ጉዳት ከፍ ያለ መሆኑን የብሪታኒያ ከፍተኛ የህክምና አማካሪ ገለፁ።
በኮቪድ 19 የመሞት እድል ከሌሎች አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን የገለፁት ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲይ ህፃናቱ ከትምህርት ቤት በመራቃቸው ግን በረጅም ጊዜ ጉዳት ያስከትልባቸዋል ብለዋል።
በርካታ ህፃናት ትምህርት ቤት በመሄዳቸው ከሚያጋጥማቸው ጉዳት ይልቅ ባለመሄዳቸው የሚያጋጥማቸው ጉዳት የከበደ ነው በማለት ተናግረዋል።
ፕሮፌሰሩ የኮሮና ቫይረስ ለቀጣዬቹ ዘጠኝ ወራት ለዓለም ስጋት ሆኖ እንደሚቀጥልም መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በ2020 የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ የመዋሉ እድሉ ዝቅተኛ መሆኑን በመግለፅ ለ2021-22 ግን ስኬታማ ክትባቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልፀዋል።
በብሪታኒያ መስከረም ወር ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱ የሚጠበቅ ሲሆን ስኮትላንድም ትምህትርት ቤቶችን ለመክፈት ዝግጅት አድርጋለች።
በብሪታኒያም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍላት ህፃናት ከሌሎች አንፃር የሚያጋጥማቸው ከባድ በሽታ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ መረጃ እንዳለ ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል።
ህፃናቱ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸው የአዕምሮ እና አካላዊ ጉዳትን በረጅም ጊዜ ውስጥ እንደሚያስከትልባቸው ጠቁመዋል።
ህፃናቱ ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸው የተወሰነ ቤተሰቦችን ወደ ስራ የሚመልስ በመሆኑ የቫይረሱ ስርጭት ላይ ሚና ሊኖር ስለሚችል አንድንድ አካባቢዎች ላይ እገዳ መጣል ተገቢ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከህፃናት ወደ ትልልቅ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የመተላለፍ እንድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ የተናገሩት ፕሮፌሰሩ የህፃናቱ ቤተሰቦች ትምህርት ቤት ላይ መገናኘታቸው ስርጭቱ ላይ አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል አልሸሸጉም።
በአጠቃላይ ትምህርት ቤት መከፈቱ የቫይረሱ ስርጭት ላይ ሚና ሊኖረው ቢችል አብዛኛው ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል።