ወሎ የአራቱ ዜማዎች ቅኝት መገኛ የሆነው አቃፊና ብዝሃነትን የማስተናገድ አቅም ስላለው ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወሎ የአራቱ ዜማዎች ቅኝት መገኛ የሆነው አቃፊ እና ብዝኃነትን በሚገባ የማስተናገድ አቅም ስላለው ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከጎርጎራ በመቀጠል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛ ፕሮጀክት የሆነውን ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ባሉ አካባቢዎች ከታሪክ ባሻገር ታሪክ ገላጭ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከየትኛው ጫፍ ጊዜውንና ገንዘቡን ሰውቶ ሐይቅ የመጣ ሰው ቢያንስ ቢያንስ ታሪክ ሳይማር፣ ፍቅር ሳይጎነጭ፣ ደስታና ሰላምን ሳይከናነብ ወደ መጣበት አይመለስም ሲሉም አውስተዋል፡፡
በሐይቅ ቆይታቸው ያስደሰታቸው የቦታው ታሪክ እና የሰው ፍቅር ብቻ ሳይሆን አየር ንብረቱ ሰላም ያለው እና የማይጠገብ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡
ወሎ የአራቱ ዜማዎች ቅኝት መገኛ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ የአራቱ ዜማዎች ቅኝት መገኛ መሆንም በዋዛ ፈዛዛ አይገኝም፤ በርካታ ታሪኮችን፣ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችንና ዘዬዎችን የማስተናገድ ልምምድ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በተለይም በአቃፊነት፣ ከሌሎች ለመማር እና ሌሎችን ለማስተማር ባለ ዝግጁነት የተፈጠረ ብቃት እና ፈጠራ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአካባቢው ያለውን ሃብት ይበልጥ ለማልማት ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ ገልጸው ÷ ለዚህም በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ለሥራው ውጤታማነት በአካባቢው ለም አፈር፣ ንጹሕ ውሃ፣ በሥራ የሚያምኑ አባቶች እና በትብብር የሚያምን ሕዝብ መኖሩን አውስተዋል፡፡
ለሎጎ ሐይቅ ግንባታ ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ በርካታ ሥራ ማከናወኑን ጠቁመው ÷ ለዚህም ሪዞርቱን እንዲያስተዳድሩ መወሰኑን ነው የገለጹት፡፡
ከሰው ማነስና ድህነት ክፉ በሽታ ነው፣ ድህነት በውጪ የሚታይ ሳይሆን በውስጥ የሚያዝና ተሸክመነው የምንሄደው ነገር ነው ብለዋል፡፡
በልባቸው እና በአዕምሯቸው ድሃ የሆኑ ሰዎች ቢያዩ እንኳን መረዳት አይችሉም፤ የልብ ስብራትን ለመጠገን ልጆች መልካም ነገር እያዩ እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
በመልካምነት ለመወሳት ልክ እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም መልካም መልካሙን ሰርቶና አስተምሮ ማለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“ኢትዮጵያ እንደ ወሎዬ ናት፤ ወሎዬ በፍቅር ሲመጡበት አርሂቡ ብሎ እጁን ዘርግቶ በፈገግታ መቀበል ይችላል፤ ነገር ግን ወሎዬ በፀብ ሲመጡበት አጋለይ ይላል፤ፀብን አንፈልግም ፀብን አንሻም፤ ፀብ ከልማት ፀብ ከብልፅግና ያስተጓጉላል፤ ጉዟችንን ያራዝማል ነው ያሉት።
የምንፈልገው እንደ ወሎየ በፍቅር የመጣውን አርሂቡ ብለን እጃችን ዘርግተን ስቀን በፈገግታ መቀበል ማጉረስ ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ነንና ደማችን ውስጥ አለና፤ በፀብ ከመጡብን ደግሞ አጋለይ እንደ ወሎዬ ማለታችን አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ጠላቶቻችን ስንስቅና ስንሰራ የደማችን ክፋይ ነውና ለአርሂቡ ዝግጁ መሆናችን፤ ስንጎነተልና ስንነካ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነን እና አጋለይ ማለት እንደምናውቅበት ልትገነዘቡ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ