Fana: At a Speed of Life!

ዳራሮ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ የሚከበር የክልሉ ድንቅ እሴት ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዳራሮ በዓል የጌዴኦ ሕዝብ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ዕሴቶችን በያዙ ስርዓቶች እና ኩነቶች ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ የሚከበር ድንቅ እሴት ነው አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ።

የጌዴኦ ብሔረሰብ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያና ተስፋ መሰነቂያ የሆነው የዕርቅና የይቅርታ በዓል “ዳራሮ” ማጠቃለያ መርሐ ግብር በዲላ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።

አቶ ጥላሁን ከበደ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ዳራሮ የጌዴኦ ብሔረሰብ የምርት መሰብሰብን ተከትሎ በራሱ የጊዜ ቀመር የአዲስ ዓመት መግባትን በማብሰር በብሩህ ተስፋ ተሞልቶ በድምቀት የሚያከብረው ታላቅ የምስጋና በዓል ነው ብለዋል፡፡

በዓሉ የጌዴኦ ሕዝብ መገለጫ የሆኑ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ዕሴቶችን በያዙ ስርዓቶች እና ኩነቶች ባህላዊ ስርዓቱንና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ የሚከበር የክልሉ ድንቅ እሴት መሆኑን ተናግረዋል።

የጌዴኦ ብሔረሰብ ተፈጥሮን በመንከባከብና በመጠበቅ እንደሀገር ለተሰነቀው የአረንጓዴ ልማት ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸው÷ ለሠላም ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለውን ይህንን ባህል ጠብቀው ያቆዩ የጌዴኦ ሕዝብን አመስግነዋል፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው÷ የበርካታ ባሕል እና ተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ፀጋዎቿን ከኢትዮጵያ አልፈው የዓለም እንዲሆኑ በማድረግ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት ብለዋል።

የጌዴኦ ሕዝብ ምርት ለሰጠ ፈጣሪ ምስጋና ከማቅረብ ባለፈ ቂምና ቁርሾን በዕርቅና ይቅርታ በመሻገር ለሀገር ሰላምና አንድነት፣ መጪው ዘመንም የበረከት ይሆን ዘንድ ተማፅኖውን የሚያደርስበት የብሩህ ዘመን ብስራት ያለው በዓል ለሀገሪቱ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.