Fana: At a Speed of Life!

የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ረገድ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ሚና

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና የመንገድ ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ነው አለ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር።

ፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የተመሰረተበት 11ኛ ዓመት የትራፊክ ህግን አክብረው ለሚያሽከረክሩ እና ለረጅም ጊዜ የትራፊክ አደጋ ሳያደረሱ ላሽከረከሩ የተቋሙ ካፒቴኖች እውቅና እና ሽልማት በመስጠትና በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሯል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አገልግሎቱ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና የመንገድ ደህንነትን በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ሚና እየጫወተ ይገኛል።

አሽከርካሪዎች የትራፊክ አደጋ የሚያስከትለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በውል በመረዳት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር ታዲዮስ ሌራ በበኩላቸው÷ አገልግሎቱ በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ለመንግሥት ሰራተኞች አገልግሎት መስጠትን ዋና ተልዕኮ አድርጎ ላለፉት 11 ዓመታት በስኬት መጓዙን አንስተዋል።

75 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ አደጋ በአሽከርካሪው የጥንቃቄ ጉድለት እንደሚደርስ አስታውሰው÷ ይህን መነሻ በማድረግና አደጋን ተከላክሎ በማሽከርከር መርህ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዓመቱን በሙሉ ምንም አደጋ ያላደረሱ አሽከርካሪዎች እውቅና መስጠትና መሸለም የበለጠ የተሻለ ስራ እንዲሰሩ በማበረታታት ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።

በመድረኩ ከ9 እስከ 7 ዓመታት ያለምንም የመንገድ ላይ አደጋ ላሽከረከሩ ከ330 በላይ የአውቶቢስ ካፒቴኖች ሽልማት እና እውቅና ተበርክቶላቸዋል።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.