Fana: At a Speed of Life!

ቴክኖሎጂ መር የትምህርት ስርዓትን ለማጎልበት …

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር ቴክኖሎጂ መር የትምህርት ስርዓትን ለማጎልበት እየተሰራ ነው አለ፡፡

ሚኒስቴሩ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ከተውጣጡ ባለድርሻዎች ጋር የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት የዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንዳሉት÷ ቴክኖሎጂ የመማር ማስተማር ተግባሩን በተሻለ ሁኔታ ለመከወን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በመሆኑም የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ለዚህም ምቹ ስነ ምህዳርን ለመፍጠር ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተቋማት መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል ተግባራት መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

የትምህርት መሰረተ ልማትን ከማስፋት አንጻር የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታና ዕድሳት በስፋት መከናወኑን ጠቅሰዋል።

የምገባ መርሐ ግብርን በማጎልበት የተማሪዎችን የትምህርት ቅበላ አቅም የማሳደግ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል።

የአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ወደ ተግባር መግባት ለትምህርት ጥራት የተሰጠው ትኩረት ያሳያል በማለት ገልጸዋል።

የመምህራንን እጥረት ለመቀነስ እና አቅማቸውን ለመገንባት ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ113 ሺህ በላይ ለሆኑ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የማጠናከሪያ ትምህርት ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው÷ ተማሪዎችን ከታች ቀርጾ ለማውጣት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በስፋት እየተሰራ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.